አራት ኢትዮጵያዊያን ዕንስት ዳኞች ወደ ሎሜ ያመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን ለመምራት ወደ ቶጎ ይጓዛሉ።

በምሮኮ አስተናጋጅነት በ2026 ለሚደረገው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተካፋይ ለመሆን ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአህጉሩ ሀገራት በቅድመ ማጣሪያ መርሀግብሩ ይካፈላሉ።

በማጣሪያው ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቤኒን ሜዳዋ በካፍ ዕገዳ የተጣለበት መሆኑን ተከትሎ የፊታችን ሐሙስ በቶጎዋ ሎሜ ከተማ በሚገኘው ስታድ ኬጉ ስታዲየም ምሽት ሁለት ሰዓት ሴራሊዮንን ስትገጥም ጨዋታውም በአራት ኢትዮጵያዊያን ዓለም አቀፍ ሴት ዳኞች እንደሚመራ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ይህንን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ሲሳይ ራያ ስትመራው በርከት ያሉ ጨዋታዎችን በአህጉሪቱም ሆነ በኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ ላይ እየመራች የምትገኘዋ ወይንሸት አበራ እና አዲሷ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ስንታየሁ ደፈርሻ በረዳትነት አራተኛ በመሆን ደግሞ መዳብ ወንድሙ ሆና ተመርጣለች።