የሊሲዎቹን ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል

በ2026 የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ዩጋንዳን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ዙርያ መግለጫ ተሰጥቷል።

ዛሬ በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2026 የሴቶች አፍሪካ ማጣርያ ከዩጋንዳ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ዙርያ ዋና አሰልጣኙ ዮሴፍ ገብረወልድ ፣ አንበሏ ታሪኳ በርገና እና የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

አስቀድመን ባጋራናቹሁ መረጃ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የቅጥር ሁኔታ ዙርያ መረጃ አድርሰናቹሁ ነበር። አሁን ደግሞ በመግለጫው የተነሱ ዋና ዋና ሀሳቦች እንደሚከተለው አሰናድተን አቅርበናል።

በመጀመርያ አሰልጣኝ ዮሴፍ ምን አሉ…..

ስለ ዮጋንዳ ቡድን ጥንካሬ ?

“የዩጋንዳ ቡድን ጠንካራ እንደሆነ ይታወቃል። ብዙ ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች አሏቸው። እነሱ የወዳጅነት ጨዋታ እንኳ ያደረጉት ከሁለት ወራት በፊት ነው። ከሞሮኮ ፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ከአልጄሪያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል። የእነዛን ጨዋታዎች ቪዲዮ አግኝተን ለማየት ሞክረናል። ምን ጠንካራ እና ምን ደካማ ጎን አላቸው ከሚለው በመነሳት ነው እየሠራን ያለነው። የዩጋንዳ ቡድን ከዚህ በፊት ከውድድር አስወጥቶናል ፤ ያ ማለት ግን አሁንም ያስወጣናል ማለት አይደለም። አጭር ቢሆንም በጣም ጠንካራ ዝግጅት አድርገናል።”

ስለጨዋታ ዕቅዳቸው ?

“ በምንችለው መንገድ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሜዳ ውጪ ስለሆነ ለዚያ የሚሆን ታክቲክ ይዘን ለመሄድ እንሞክራለን። ስንመለስ ደግሞ ጨዋታው በሜዳችን ስለሆነ ትልቁን ነገር እዛው ጨርሰን ለመምጣት እንሞክራለን። ትልቁ ነገር የምንችለውን ነገር ሜዳ ላይ ለማድረግ እንሞክራለን።”

ከሀገር ውጭ ስለተጠሩ ተጫዋቾች ?

“አርያት ኦዶንግ ፣ አረጋሽ ካልሳ እና ሎዛ አበራን ከሀገር ውጪ ልምድ ይዘው ስለሚመጡ በሚል ጠርተናል። አርያት በጉዳት ምክንያት መምጣት አልቻለችም። አረጋሽ ከመኖሪያ ፍቃድ ጋር በተገናኘ ብዙ ጌም ላይ አልነበረችም። ግን በገባችበት ጌም ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ታደርግ ስለነበር ጠርተናታል። በሎዛ በኩል ደግሞ አሜሪካ ውድድሩ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቅቆ ለሁለተኛ ዙር ዝግጅት ላይ ነበሩ ገና ቅዳሜ ነው የሚጀምሩት እና የሚያጠያይቅ ነገር ስለሌለ እና ትልቅ ተጫዋች ስለሆነች እንደምትጠቅመንም ስለምናውቅ ነው እንድትመጣ ያደረግነው። ፌዴሬሽኑ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሎ ነው የእሷን መምጫ ሁሉ ሸፍኖ የመጣችው በዚህ አጋጣሚ ፌዴሬሽኑንም ልናመሰግን እንወዳለን።”

ስለ ዮጋንዳ ቡድን ስብስብ ?

“ዩጋንዳዎች ጥሪ ካደረጉላቸው 39 ተጫዋቾች 10 የሚሆኑት ከውጪ የመጡ ናቸው። በሕንድ ሊግ 2 ( በ9 እና በ7 ጎል ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን የሚመሩ ናቸው። በዴንማርክ እና በሌላ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሏቸው። ይህም ጥንካሬያቸውን እና ምን ያህል እየሠሩ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ስለዚህ በምንችለው መንገድ ተፎካካሪ ሆነን ለመምጣት እና ቡድናችንን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማሳለፍ እንሞክራለን ብዬ አስባለሁ።”

አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የአፍሪካ ዋንጫ የማያሳልፉ ከሆኖ እንደሚሰናበቱ ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ ባህሩ ሲመልሱ

“እኛ ውል ገብተናል አስገዳጅ ነገሮች ይኖሩታል። ለአስገዳጅ ነገሮች ደግሞ ፌዴሬሽን ማድረግ የሚገባውን ድጋፍ ማድረግ ማገዝ የሚገባውን  ነገር  ማገዝ ይፈልጋል። እኛ ለአፍሪካ ዋንጫ አናልፍም ብለን አናስብም ለአፍሪካ ዋንጫ እናልፋለን ብለን ነው የምናስበው። መልካም የሆነ አመለካከት ነው ያለን ። ስለምናልፍ ያ አስገዳጅ ነገሩ ብዙም ችግር አይፈጥም የሚለውን ሀሳብ ለመስጠት ነው። ከዚህ አንፃር እንድናየው እፈልጋለው።”