በሊጉ መሪ የጀመረው የዐበይት ጉዳዮች መሰናዷችን ዛሬም በፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያ የውድድር ዘመናቸው ላይ የሚገኙ ተስፈኛ ተጫዋቾች ትኩረቱን አድርጓል።
ሀገሪቱ ያለው የክለቦች የዝውውር አካሄድ በርከት ያሉ ወጣት ተስፈኞች እንዳይፈሩ እክል ሆኗል! የዛሬን አያደርገውና በሊጋችን የውጭ ተጫዋቾች ከመበራከታቸው በፊት በቁጥርም ሆነ በጥራት በርከት ያሉ ወጣት ተስፈኞች የሚፈሩበት ነበር።
ሆኖም አሁንም የተሰጣቸው ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ያሳዩ የቀጣዩ ዘመን ከዋክብት ጥቂት አይደሉም።
የዐፄዎቹ ተስፋ አንዋር ሙራድ !
አሰልጣኝ ውበቱ በአዲስ ቡድን ግንባታ ለገጠማቸው ውጣ ውረድ መፍትሔ ሆነው ብቅ ካሉ ወጣት ተጫዋቾች አንዱ ነው። በግማሽ ዓመቱ የ375 ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ቆይታ ያለው ተስፈኛው በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ለዐፄዎቹ ወሳኝ ነጥቦች ያስገኙ ግቦች ከማስቆጠሩ በዘለለ ያለው የጎል ርሀብ እና ቅልጥፍና ለወደፊቱ ትልቅ ተስፋ እንዲጣልበት ያደርጋል። በመጀመርያው ዙር ካገኘው የጨዋታ ዕድል አንፃር ሲታይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሰጠው አንዋር ዐፄዎቹ የሁለተኛው ዙር ጉዟቸው እንዲያቃኑ ተስፋ ከሚያደርጉባቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው።
የምዓም አናብስቱ የጭንቅ ቀን ደራሽ ዘርእሰናይ ብርሀነ !
ዘርእሰናይ ብርሀነ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ወሳኝ ተከላካዮቻቸው በጉዳት ባጡባቸው ሳምንታት አለው ያለ የጭንቅ ቀን ደራሽ ነው። በፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያ ዓመት ላይ የሚገኘው ወጣቱ ከዕድሜው ጋር በማይመጣጠን ጥንካሬው በ16 ጨዋታዎች ተሰልፎ 1436 ደቂቃዎች እናት ክለቡን አገልግሏል። ከአሸናፊ ሀፍቱ በኋላ ከታዳጊ ቡድናቸው ወጥቶ በዋናው ቡድን ደረጃ በቋሚነት የሚያገለግል ተጫዋች ያላገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ከዓመታት በኋላ በተመለሱበት ሊግ ለቀጣይ ተስፋ ያለው ተከላካይ ይዘው ብቅ ብለዋል።
ከኮረቻው ተረካቢዎች አንዱ መሆኑን ያስመሰከረው ፈረሰኛው ሔኖክ ዮሐንስ
ወጣት ተጫዋቾች በማሰለፍ በቅድሚያ ከሚጠቀሱ ክለቦች አንዱ በሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በርከት ያሉ ተስፈኛ ተጫዋቾች ይገኛሉ። አብርሀም ታምራት ፣ ሻይዱ ሙስጠፋ እና ብሩክ ታረቀኝ በውድድር ዓመቱ ራሳቸውን ብቁ አድርገው አሳዳጊ ክለባቸውን በወጥነት በማገልገል ይገኛሉ። ሔኖክ ዮሐንስ ግን ፈረሰኞቹ በውድድር ዓመቱ ያስተዋወቁት አዲሱ የመጪው ዘመን ተስፋ ነው! ተስፈኛው የመስመር ተከላካይ በውድድር ዓመቱ ጅማሮ ቦታውን ማስከበር ተቸግሮ የቆየ ቢሆንም በተከታታይ በቋሚነት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ብቃት አሳይቶ ቦታውን አፅንቷል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሰጡትን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ላይ የሚገኘው ተስፈኛው በቀጣይ ከሊጉ ምርጥ የመስመር ተከላካዮች መደብ ሊያሰልፈው የሚችል አቅም እንዳለውም አሳይቷል።
ተስፈኛው የግብ ዘብ ዮሐስን ደርሶ!
ፋሲሎች ናይጀርያዊው ግብ ጠባቂ አማስ ኦባሶጊ እንዲሸጡ መተማመኛ የሆናቸው እና በውድድር ዓመቱ ይበልጥ ራሱን ያሳደገው ዮሐንስ ደርሶ በለጋ ዕድሜው ከፍተኛ ልምድ በሚጠይቀው የግብ ጠባቂነት ቦታ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል። በውድድር ዓመቱ በስድስት ጨዋታዎች ተሳትፎ 540 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው ወጣቱ ተጫዋች ለቀጣይ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ግብ ጠባቂ እንደሚሆን በማሳየት ላይ ይገኛል።
ከተጠበቀው በላይ የደመቀው በረከት ካሌብ!
በጠንካራው የመድን ተከላካይ ክፍል የበኩሉን ድርሻ የተወጣው በረከት ካሌብ በመንፈቁ በወጥነት ቡድናቸው ካገለገሉ ተስፈኞች አንዱ ነው። ከዚህ ቀደም በተመስገን ዳና እየተመራ እስከ ፍፃሜ ድረስ የተጓዘው የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን አባል የነበረው፤ በሀዋሳ ከተማና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጣት ቡድኖች ውስጥ የተጫወተው እና በፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያ ዓመት ላይ የሚገኘው ይህ ተስፈኛ የመስመር ተከላካይ በጠንካራው የሊጉ የመከላከል ጥምረት ውስጥ በ13 ጨዋታዎች ተሰልፎ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይቷል። በተሳተፈባቸው ጨዋታዎች ያሳየው ተስፋ ሰጪ እና ተከታታይነት ያለው ብቃትም በተስፈኛ ከዋክብት ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።
ሄኖክ ይበልጣል የጣና ሞገዶቹ አዲስ ግኝት!
ለአንድ ወጣት ተጫዋች በማንኛውም ቦታ ላይ ተሰልፎ መጫወት ከባድ ቢሆንም የጥልቅ አማካይነት ሚና ግን ከሁሉም የላቀ ልምድ እና ኃላፊነት የሚጠይቅ ቦታ ነው። በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ አሳዳጊ ክለቡን በማገልገል ላይ የሚገኘው ሄኖክ ይበልጣል ግን አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው የሰጡትን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ለቦታው የሚመጥን ብቃት እንዳለው አስመስክሯል። በአጭር ጊዜ የዋናው ቡድን ቆይታው ከወዲሁ በጣና ሞገዶቹ ደጋፊዎች ልብ መግባት የቻለው አማካዩ በቀጣይ ዓመታት በትልቅ ደረጃ የመጫወት አቅም እንዳለው አሳይቷል።
በቡናማው ቤት የደመቀው የጋምቤላው ፈርጥ ኦካይ ጁል
በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ቡናማዎቹን ተቀላቅሎ ከቡድኑ ጋር ጥሩ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው አማካዩ ኦካይ ጁል በመጀመርያው ዙር ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረጉ ወጣት አማካዮች አንዱ ነው። ከዚህ ቀደም በጉለሌ ክፍለከተማ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሀላባ ከተማ የተጫወተው እና ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሊግ ምርጥ ቡድን ውስጥ መካተት የቻለው ይህ ተስፈኛ አማካይ በቡናማው መለያ ባከናወናቸው 13 ጨዋታዎች ያሳየው ጥሩ ብቃት ከቀጣይ ዘመን የሊጉ ከዋክብት አንዱ መሆኑ አስመስክሯል።
የቢጫዎቹቹ ሱልጣን በርኸ እና ናሆም ኃይለማርያም
በሊጉ ግርጌ ከተቀመጡት ወልዋሎዎች አወንታዊ ነጥብ ካነሳን የሁለቱም ስም ማንሳት ግድ ነው፤ ሱልጣን በርሐ እና ናሆም ኃይለማርያም! በውጤት ማጣት ቀውስ በተፈተነው ቡድን ውስጥ በየፊናቸው ስምንት ስምንት ጨዋታዎች ያከናወኑት ወጣቶቹ የመስመር ተከላካዮች በግማሽ የውድድር ዓመት በግላቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርገዋል።በመጀመርያው ዙር ጎልተው ከወጡ የሊጉ ተስፈኛ ተጫዋቾች መሀል የሚጠቀሱት ተጫዋቾቹ በሁለተኛው ዙርም እናት ክለባቸውን ከመውረድ የመታገድ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።