ከሁለት የጨዋታ ሳምንታት በላይ ያልዘለቀው የወልቂጤ ከተማ የሊጉ ቆይታ…
የእግር ኳሳችን የፋይናንስ ሁኔታ በጠና ከታመመ ሰንበትበት ብሏል። ክለቦች ቅጥ ባጣ የገንዘብ አወጣጥ መንገዳገድ ከጀመሩ ቀላል የማይባል ጊዜያት ቢቆጠሩም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን አካሄዳቸው ከመንገዳገድ አልፎ ጠልፎ እየጣላቸው ነው።
ለዓመታት የዘለቀ ሲወርድ ሲዋረድ የቆየ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የነበረው ወልቂጤ ከተማ ያለፉትን ዓመታት ተቸግሮም ቢሆን የፕሪምየር ሊግ ህልውናውን ቢያስቀጥልም ዘንድሮ ግን ‘የክለብ ላይሰንሲንግ’ ምዝገባ ባለማገባደዱ በውድድሩ ጅማሮ ከሊጉ መሰናበቱ በመጀመሪያው ዙር በስፋት አነጋጋሪ ከነበሩ ዓበይት ጉዳዮች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት በመቻል እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፎርፌ ከተሸነፈ በኋላ ከሦስተኛው ሳምንት በኋላ ከሊጉ የተሰናበተው ቡድኑ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርቶች ባለማሟላት ከፕሪምየር ሊጉ የተሰናበተ የመጀመሪያው ክለብ መሆኑ ይታወሳል። የሊጉ መርሐግብር በሦስት አጋጣሚዎች እንዲለወጥ እንዲሁም ሊጉ በ18 ክለቦች መካከል እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው የሰራተኞቹ ጉዳይ ባለፉት ወራት በሀገሪቱ እግር ኳስ ዋነኛ መነጋገርያ ነጥብም ነበር።
የዘንድሮው የወልቂጤ ከተማ ጉዳይ ክለቦች አባካኝነት የተሞላበት የገንዘብ አጠቃቀም መንገዳቸውን እንዲቀይሩ እና አደጋ ላይ ላለው ሕልውናቸው መፍትሔ እንዲያበጁ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ጉዳይ ሆኗል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ግን የብዙ ክለቦች ሕልውና ታሪክ ሆኖ መቅረቱን ለመገመት ነብይ መሆን አይጠበቅብንም።