የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር 6ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ከቀናት በኋላ ያከናውናል።
ከተመሰረተ አምስት ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ ዕርከን ውድድር በበላይነት እየመራ እንደሚገኝ ይታወቃል። አክሲዮን ማኅበሩ የ2017 የውድድር ዓመት መጋመሱን አስመልክቶ የፊታችን እሁድ የካቲት 16 በሂልተን ሆቴል 6ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።
በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ በዋናነት የመመስረቻ ፅሁፍ ላይ ማሻሻያ ማድረግ፣ ለዳይሬክተሪች ቦርድ የስራ ዋጋ እና አበል ማስወሰን እንዲሁም የ2017 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዙር አጠቃላይ ግምገማ ማድረግ የሚሉ አጀንዳዎች ያሉ ሲሆን ምናልባት ከተጫዋቾች ዝውውር እና የክለቦች ክፍያ አስተዳደር መመሪያ አተገባበር ጋር ተያይዞ ሀሳቦች ሊንሸራሸሩ እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።