የአሰልጣኞች ራስ ምታት ሆኖ የከረመው የተጫዋቾች ጉዳት……
በአስራ ሰባቱ የጨዋታ ሳምንታት ውስጥ ከተፈጠሩ ዐበይት ክስተቶች ውስጥ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት አንዱ ነው። በውድድር ዓመቱ እንደ ትልቅ አጀንዳ ብዙ ያልተወራለት ነገር ግን በሊጉ ፉክክር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የፈጠረው የተጫዋቾች ጉዳት ሁሉንም የሊጉ ክለቦች በሚባል ደረጃ ጎብኝቷል።
እግር ኳስ ፈጣን እና ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቅ ስፖርት እንደ መሆኑ ጉዳቶችም የተለመዱ ቢሆኑም ዘንድሮ ግን በቅርብ ዓመታት ከነበረው የተጫዋቾች ጉዳት መጠን ላቅ ያለ ነው። በሊጉ ለሚታየው ተደጋጋሚ ጉዳት ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም የጨዋታዎች መደራረብ እና በቂ የማገገምያ ጊዜ እጥረት እንዲሁም የመጫወቻ ሜዳው አለመመቸት ለችግሩ እንደ ዋነኛ ጠንቅ ተደርገው ይነሳሉ። ሜዳዎች እውን ለተጫዋቾች ጉዳት ዋነኛ መንስኤ ናቸው ብሎ ለመደምደም ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም በግርድፉ ስናየው ግን ብዙ ቅሬታዎች የቀረቡባቸው ስታዲየሞቻችን ለጉዳት የሚያጋልጡበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
ሜዳዎች ኳስ ለማንከባለል የማይመቹ መሆናቸው
እንዲሁም ብዙ ኃይል የሚጠይቁ መሆናቸው ለጉዳት ከማጋለጣቸው በዘለለ የጨዋታዎች መደረረብ ተጫዋቾች ያለ በቂ ማገገሚያ ጊዜ ጨዋታዎችን ለማድረግ መገደዳቸውም ሌላው ፈተና ነው። ተጫዋቾች ከባለፉት ዓመታት በተለየ በገጠማቸው የመርሐግብሮች መደራረብ ከፈጠረው አካላዊ ዝለት በተጨማሪ የአዕምሮ ጫናውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህ ጋር ተያይዞም ተጫዋቾች ለጉዳት ተጋላጭ የሚሆኑበት ዕድል እንደሚያሰፋው ይታመናል። የድሬዳዋ ስታዲየም በእራሱ በብዙኃኑ ዘንድ ለጨዋታ ምቹ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ቢነሳም ወድድሩ በድሬዳዋ በተደረገበት ወቅት የደረሱ የጉዳቶች ብዛትን ለተመለከተ ግን የተለመደውን የሰው ሰራሽ ሜዳዎች እና የተጫዋቾች ደህንነት ጉዳይን ለማንሳት ያስገድደናል። ሁለተኛው ዙር ለዋንጫ እንዲሁም ላለመውረድ ወሳኝ መርሐግብሮች የሚደረጉበት ወቅት እንደመሆኑ የፍልሚያው ጫፍ አንድ ደረጃ ከፍ ማለቱ አይቀሬ ነው። ይህንን ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር ከታየው ነገር አንጻር ብዙ ተጫዋቾች ለዚህ ችግር እንደሚጋለጡ መገመት ይቻላል።
ለማሳያ ያህል ጥቂት ክለቦች እናንሳ
በመግቢያው ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሁሉም የሊጉ ክለቦች በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት ሰለባ ነበሩ፤ ሆኖም ጉዳት የበረታባቸውን ክለቦች በወፍ በረር ለመቃኘት እንሞክራለን።
3 ጨዋታዎች ብቻ ያከናወነው አበበ ጥላሁን እና 2 ጨዋታዎች ብቻ ያደረገው ሳሙኤል አስፈሪን ጨምሮ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር የተለያየው ስቴፋን ባዱ አዬርኬ ዘለግ ላሉ የጨዋታ ሳምንታት ያጡት አርባምንጭ ከተማዎች ጉዳት የተከላካይ ክፍላቸውን ክፉኛ ደቁሶታል፤ በውድድር ዓመቱ 20 ግቦች ለማስተናገድ የተገደደው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሳምንታትም ወሳኙን አጥቂ አሕመድ ሔሴን በጉዳት አጥቷል። በአስራ ስድስት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማም ወሳኙ ተጫዋች ቢኒያም ዐይተን፣ ዳንኤል ደምሱ እና ፍቃዱ ደነቀ እንዲሁም አድናን ረሻድ ለበርካታ ሳምንታት በጉዳት ያጣ ክለብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ በአስከፊ ጉዳት እያሱ ለገሰን እስከ ውድድር ዓመቱ ፍፃሜ ያጡት እና በጉዳት ምክንያት ከናትናኤል ዘለቀ በቂ ግልጋሎት ያላገኙት ወልዋሎዎች እንዲሁም በከባድ የጭንቅላት ጉዳት መክብብ ደገፉን ለረዥም ሳምንታት በጉዳት ያጡት ሲዳማ ቡናዎችም የረዥም ጊዜ ጉዳት ከጎበኛቸው ቡድኖች ውስጥ ናቸው።
በጉዳት ምክንያት በየፊናቸው አንድ አንድ ጨዋታ ብቻ ያከናወኑት መናፍ ዐወል እና ዮናስ ግርማይን ጨምሮ አማካዩ የአብሥራ ተስፋዬ እና አሸናፊ ሀፍቱ በርከት ባሉ የጨዋታ ሳምንታት ያጣው መቐለ 70 እንደርታ ሌላው በተጫዋቾች ጉዳት የተጠቃ ቡድን ሲሆን ቁልፍ ተጫዋቾቹ ፉዓድ ፈረጃ እና ሱሌይማን ሐሚድ ለረዥም ጊዜያት በጉዳት ያጣው ቻምፒዮኑ ንግድ ባንክም ሌላው ተጠቃሽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የመሐመድኑር ናስር ጉዳት የውድድር ዓመቱን መልክ የቀየረበት ድሬዳዋ ከተማ እናንሳ፤ በመጀመሪያዎቹ 9 የሊግ መርሐግብሮች 14 ግቦች ካስቆጠሩ በኋላ 6 ግቦች ያስቆጠረው ወሳኙ አጥቂያቸው በጉዳት ያጡት ብርቱካናማዎቹ ተጫዋቹ በጉዳት ባጡባቸው ሰባት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻሉት የግብ መጠን ሦስት ብቻ መሆኑን ስናይ ጉዳት ምንያህል በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ መገንዘብ ይቻላል።
በአንድ ወቅት ተቀዳሚ ግብ ጠባቂያቸው ቢኒያም ገነቱ እና ሁለተኛ ተመራጩ አብነት ይስሃቅ በጉዳት አጥተው በሦስተኛ ግብ ጠባቂያቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ለማከናወን የተገደዱት እና የግብ ጠባቂ አማራጭ ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች፤ ቋሚ ተሰላፊዎቻቸው አፍቅሮተ ሰለሞን እና አቤል እንዳለ እንዲሁም ኪሩቤል ዳኜ ዘለግ ላሉ ሳምንታት በጉዳት ያጡት ፋሲል ከነማዎች፤ ረዘም ላለ የጨዋታ ሳምንታት አብዲሳ ጀማል እና ካይዋ በጉዳት ያጡት መድኖች እንዲሁም ለረዥም ጊዜ የጫላ ተሺታን ግልጋሎት ያላገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎችም ተጠቃሾች ናቸው።
የተጫዋቾች ጉዳት ገፈጥ ቀማሽ የሆኑት አሰልጣኞች ከጨዋታዎች በኋላ በሰጧቸው አስተያየቶች ይህንን የተጫዋቾች ጉዳት ተደጋጋሚ ጊዚ አንስተውታል። በመጀመርያው ዙር ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት በተሟላ ስብስብ ወደ ጨዋታዎችን እንዳይቀርቡ ያገዳቸው ሲሆን በሁለተኛው መንፈቅ በምን ዓይነት መንገድ ችግሩን ቀርፈው ይቀጥላሉ የሚለው ጉዳይም ትልቁ የቤት ስራቸው ይሆናል።