ሪፖርት | ዩጋንዳ በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች ኢትዮጵያን አሸንፋለች

በሞሮኮ በሚደረገው የ2026 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሉሲዎቹ በዩጋንዳ የ2ለ0 ሽንፈት አስተናግደዋል።

በካሜሮናዊቷ የመሐል ዳኛ ማሪ ጆሴፍ መሪነት በጀመረው የሁለቱ ሀገራት የማጣሪያ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩትም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራን አላስመለከተንም። ረጃጅም ኳሶችን ከሁለቱ መስመሮች መነሻቸውን በማድረግ ወደ ሳጥን መጣልን ምርጫቸው ያደረጉት ዩጋንዳዎች የመጨረሻው ሜዳ ላይ የሚያደርሷቸውን ኳሶች ለመጠቀም የሉሲዎቹን የኋላ ክፍል አስከፍቶ መግባት ላይ ውስንነት ነበረባቸው።

ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያውን በመስጠት ባነሰ የማጥቃት ቁጥር በተወሰነ መልኩ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በቀላሉ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያኑ ዕንስቶች 31ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ ስል ተብላ ልትጠቀስ የምትችል አጋጣሚን ፈጥረዋል። ሴናፍ ዋቁማ ራሷ ያስቀጠለችውን ኳስ ሎዛ አበራ አመቻችታ ስታቀብላት ጥድፊያ በታከለበት እንቅስቃሴ ከሳጥን ውጪ አጥቂዋ ሙከራ አድርጋ ለጥቂት አጋጣሚዋ ወደ ውጪ ወጥታ አጋማሹም ያለ ጎል ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ዩጋንዳዎች አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች በተለይ በሽግግር አጨዋወት ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም የግብ ዘቧ ታሪኳ በርገናን የነቃ የግብ አጠባበቅን አልፎ ግብ ማስቆጠሩ ከብዷቸው ታይቷል። ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴን በመጠቀም በተወሰነ መልኩ መልሶ ማጥቃት ላይ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሉሲዎቹ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ቢወሰድባቸውም በቀላሉ ግን ግባቸውን አሳልፎ ላለመስጠት ጥረቶች አልተለያቸውም። ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ ሁለቱም ሀገራት አከታትለው በተመሳሳይ የሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ካደረጉ በኋላ በቀጠለው ጨዋታ 66ኛው ደቂቃ ላይ ጥራት ያላትን ሙከራ ዩጋንዳዎች አስመልክተውናል።

ከቀኝ መስመር በኩል ወደ ውስጥ የተሻገረን ኳስ ፒዮና ናቡምባ ወደ ግብ ስትመታ ታሪኳ በርገና ያዳነቻት ዒላማዋን የጠበቀች አደገኛ አጋጣሚ ሆናለች። 84ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ምርቃት ፈለቀ ከግራ በረጅሙ ያሻገረችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ተቆጣጥራ ከጠባብ አንግል ያደረገቻት ሙከራ በሩዝ አቱሮ ከተመለሰባት በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች በድግግሞሽ ማጥቃቱ ላይ የበረቱት ዩጋንዳዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎሎችን አስቆጥረዋል።

90ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ብርቄ አማረ በሠራችው ጥፋት የተሰጠን የቅጣት ምት ዛይናህ ናሙሌሜ አክርራ መታ መረቡ ላይ ኳሷን በማስቀመጥ ዩጋንዳን መሪ ስታደርግ ከሦስት ደቂቃዎች መልስ ደግሞ ፍፁም የመከላከል ድክመት የታየባቸውን የኢትዮጵያ ተከላካዮችን በብልጠት ያለፈችው ፋዚላ ኢኩዋፑት ሌላ ግብ በማከል ጨዋታው በመጨረሻም በዩጋንዳዊያን ዕንስቶች 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

 

የመልሱ ጨዋታም የፊታችን ረቡዕ የካቲት 19 በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።