በግማሹ የውድድር ዓመት ምርጡ ውህደት የነበረው የኋላ ጥምረት…
በጥምረት ረገድ እንደ የኢትዮጵያ መድን የተከላካይ ክፍል ውጤታማ ጊዜ ያሳለፈ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው ብንል የቃሉ ግነት እምብዛም ነው። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የገነቡት የኋላ ክፍል ብቃት የሚገባውን ያክል ሙገሳ እና በቂ ሽፋን አግኝቷል ለማለትም አያስደፍርም። የመከላከል አደረጃጀቱ በመጀመሪያው ዙር በተከናወኑ 17 ጨዋታዎች 5 ግቦች ብቻ በማስተናገድ በ 12 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ችሏል። ጥቂት ግቦች በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃነት ከተቀመጡ ክለቦች በ 6 ያነሰ የግብ መጠን ያስተናገደው ጥምረቱ ከተቆጠሩበት 5 ግቦች ውስጥ 3ቱ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የተቆጠሩ መሆናቸው ሲታሰብ ደግሞ ምን ያህል ውጤታማ ጊዜ እንዳሳለፈ ተጨማሪ ማሳያ ነው።
እርግጥ ነው መድን እንደ ቡድን ውጤታማ ጊዜ አሳልፏል ይሄ ግን የተከላካይ ክፍሉ ተነጥሎ ከመሞገስ ሊያስቀረው አይገባም፤ ቁጥሮች ጥምረቱ ድንቅ የውድድር ዓመት እንዳሳለፈ በቂ ምስክር ናቸው። በእግርኳስ ሕይወቱ ምርጡን ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኘው እና በሊጉ እያንዷንዷን ደቂቃ ሜዳ ላይ የቆየው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ፤ ፊት አውራሪው ሚሊዮን ሰለሞን፣ ጥሩ የውድድር ዓመት በማሳለፍ የሚገኙት ወጣቶቹ ያሬድ ካሳዬ እና በረከት ካሌብ እንዲሁም ከሚታወቅበት የአማካይነት ቦታ ወደ ኋላ ተመልሶ የተዋጣለት የመሃል ተከላካይ የሆነው ንጋቱ ገብረሄላሴ የጥምረቱ ወሳኝ ተጫዋቾች ሲሆኑ ምንተስኖት አዳነ፣ ዋንጬ ቱት፣ አዲስ ተስፋዬ፣ ዳግማዊ ዓባይ፣ ያሬድ መሐመድ፣ ረመዳን ሑሴን እና ዮሐንስ ሴጌቦ ደግሞ በመከለከል ጥንካሬው የበኩላቸውን የተወጡ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው።