ከሁለት ቀናት በፊት ከስሑል ሽረ ጋር የተለያየው ግብ ጠባቂ ሌላኛውን የሊጉ ክለብ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።
ስሑል ሽረን ለመልቀቅ ካቀረበው ጥያቄ በኋላ ከቡድኑ ጋር በስምምነት የተለያየው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስሙ ቢያያዝም በስተመጨረሻም ፋሲል ከነማን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሷል።
ባለፈው ወር ከናይጄሪያው ግብ ጠባቂ አማስ ኦባሶጊ ጋር የተለያዩት ዐፄዎቹ በቦታው ያለባቸውን ክፍተት ፋሲል ገብረሚካኤል ይሸፍናል ብለው ይጠብቃሉ። በአብዛኞቹ ነገሮች ከስምምነት በደረሱት ክለቡ እና ተጫዋቹ በቀጣይ ጊዜያት የወረቀት ሥራዎች ሲጠናቀቁ ተጫዋቹ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዋናው እና ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ጨምሮ በደደቢት፣ ሰበታ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ስሑል ሽረ የተጫወተው ግብ ጠባቂው በዝውውር መስኮቱ ለፋሲል ከነማ የፈረመ የመጀመሪያው ተጫዋች ለመሆን ተቃርቧል።