አበባው ቡታቆ እና ሲሳይ ባንጫ ቅጣት ተላለፈባቸው

አበባው ቡታቆ እና ሲሳይ ባንጫ ቅጣት ተላለፈባቸው

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በሆኑት አበባው ቡጣቆ እና ሲሳይ ባንጫ ላይ ቅጣት ማስተላለፉን ዛሬ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

በአለም ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታ የመልስ ግጥሚያ ላይ የተሰለፉት ሁለቱ ተጫዋቾች በናይጄሪያ ካላበር በነበሩበት ወቅት ሁለቱ ተጫዋቾች መጣላታቸውን መሰረት በማድረግ ነው ቅጣት የተላለፈባቸው፡፡

የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ክፍል 3 አንቀጽ 33 ንዑስ አንቀጽ 33 የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር መሰረት በማድረግ በሁለቱ ተጫዋቾች ላይ ቅጣት ማስተላለፉን በላከው መግለጫ ላይ አመልክቷል፡፡

በዚህም መሰረት ግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ የ10 ሺህ ብር ቅጣት እና የዚህ ዓይነት የስነምግባር ግድፈት ወደፊት እንዳይፈጽም ከባድ የጽሁፍ መስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ሁለተኛው ተጫዋች አበባው ቡታቆ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እና የዚህ አይነት ጥፋት ወደፊት እንዳይፈጽም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሰው መደረጉን ፌዴሬሽኑ በላከው መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን ያስተላለፈው በወቅቱ ሁለቱ ተጫዋቾች ሲጣሉ በቦታው የነበሩትን የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና ተጫዎቾች ጠርቶ ስለጉዳዩ የምስክርነት ቃለቸውን በማድመጥ እንዲሁም እራሳቸው ሁለቱ ተጫዋቾችን ጠርቶ በማናገር መሆኑ ተገልጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ