የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ተካሂዶ ለቀጣዮቹ 40 ቀናት ተቋርጧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ትናንት እና ዛሬ ተካሂዶ ለቀጣዮቹ 40 ቀናት ተቋርጧል፡፡

ቅዳሜ እለት በተካሄደው ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኤልያስ ማሞ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ መድንን 1-0 አሸንፎ ነጥቡን 18 አድርሷል፡፡ ጨዋታው ብዙም ሳቢ ያልነበረ እና በሙከራዎች ያልታጀበ ሲሆን ኤልያስ ማሞ ግብ ከማስቆጠሩ በፊት ፊሊፕ ዳውዚ ከርቀት አክርሮ የመታውና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ልትጠቀስ የምትችል ሙከራ ነበረች፡፡

ዛሬ በተካሄዱት የ9ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ሀዋሳ ላይ የተካሄደውና ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የሀዋሳ ከተማ እና ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ ይርጋለም ላይ የተጫወቱት ሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ካለግብ ተለያይተዋል፡፡

አሰልጣኙን ያሰናበተው የ3 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ መብራት ኃይል በሙገር ሲሚንቶ 2-0 ተሸንፎ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየሙ ጨዋታ ጋናዊው ጌድዮን አካክፖ እና ናይጄያዊው አኪም አካንዴ የአሰላውን ክለብ ግቦች አስቆጥረዋል፡፡

የአዲስ መጪዎቹ ዳሸን ቢራ እና ወላይታ ድቻ፣ የደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና እና የሐረር ቢራ ጨዋታ ዳሸን ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለብሄራዊ ቡድን 3 እና ከዛ በላይ ተጫዋቾች በማስመረጣቸው ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡

ሊጉን 3 ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ18 ነጥብ ሲመራ ፤ 9ኙንም ጨዋታዎች ያደረገው የፀጋዬ ኪዳነማርያም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ 2 ደረጃን ይዟል፡፡ መብራት ኃይል ደግሞ በ5 ነጥብ የመጨረሻው 14 ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኡመድ ኡኩሪ በ6 ግቦች ሲመራ የንግድ ባንኩ ፊሊፕ ዳውዚ በ4 ይከተላል፡፡

ሊጉ በቻን ዝግጅት እና ጨዋታዎች ምክንያት ለ40 ቀናት ሲቋረጥ የካቲት 1 እና 2 ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ ፤ አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ ሐረር ቢራ ከ ሲዳማ ቡና ፤ ሙገር ሲሚንቶ ከ ኢትዮጵያ ቡና ፤ ዳሸን ቢራ ከ መብራት ኃይል ፤ ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ድቻ ፤ መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚያደርጉት የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ