ክለብ ዳሰሳ – መከላከያ

ጦሩ ከባዱን የውድድር ዘመን በድል ይወጣል?

የውድድር ዘመኑን በጥሎማለፍ ድል የከፈተው መከላከያ ከመልካም አጀማመር በኃላ እውነተኛው ፈተና ላይ ደርሷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ የዘንድሮውን የውድድር ዘመን የመከላከያ ጉዞ በሚዳስሰው ፅሁፍ የክለቡን ተስፋ እና እንቅፋት ለመዳሰስ ትሞክራለች፡፡

ታሪካዊው ክለብ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከተቀላቀለ ዘንድሮ 10 የውድድር ዘመኑን ጀምሯል፡፡ማራኪ አጨዋወትን ከባለ ክህሎት ተጫዋቾች ጋር ያጣመረው መከላከያ ዘንድሮ ጥቂት ግን የብልሃት ውሳኔ የታከለበት ዝውውር አድርጎ የተጠናከረ ስብስብ ይዞ ቀርቧል፡፡ በውድድር ዘመኑ መጀመርያ ያደረጉት 2005 የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜም መከላከያ የዋንጫ ተፎካካሪ ይሆናል ብለን እንድንገምት የሚያስገድድ ጨዋታ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው የዋንጫ ባለቤት በሆኑበት ጨዋታ ምንም እንኳን ቅዱስ ጊዮርጊስ 2/3ኛውን ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ ቢጫወትም መከላከያ በኃይል የተሞላ ጨዋታውን ለማሸነፍ ቁርጠኛ የነበረ እና በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ነበር፡፡ ቡድኑ ፕሪሚየር ሊጉን በድል ቢምርም ቀስ በቀስ መንሸራት ጀምሯል፡፡ ያለፉትን 5 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ብንመለከት እንኳን መከላከያ ድል ያደኘው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ ዘንድሮ በአፍሪካ ውድድር 7 አመታት በኃላ ለሚሳተፈው መከላከያ ቀጣዮቹ 2 ወራት የውድድር ዘመኑን ጉዞ የሚወስኑ ጠንካራ ጨዋታዎች ይገጥሙታል፡፡

ተስፋዎች

ቋሚ ተሰላፊዎች

የመከላከያ ቋሚ ተሰለፊዎች ድንቅ ናቸው፡፡ ቋሚ አስራ አንዱ በሊጉ ለመፎካከር በቂ ከመሆኑ በላይ ለበርካታ ጨዋታዎች የማይቀየር በመሆኑ በሚገባ ተዋህዷል፡፡ ለረጅም ጊዜያት በክለቡ የቆየው ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ዘንድሮ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ የአንድ ለአንድ አጋጣሚዎች እና ፍፁም ቅጣት ምቶች ላይ ብቃት ድንቅ ነው፡፡ ዘንድሮ የፈረሙት ሲሳይ ደምሴ እና ተስፋዬ በቀለ ቦታቸውን አስከብረዋል፡፡ በአማካይ ክፍል የአብርሃም ይስሃቅ ሚካኤል ደስታ ፍሬው ሰለሞን እና ጥላሁን ወልዴ ጥምረት እና የማናዩ ፋንቱ ከአማካዮች ጋር ያለው መናበብ ድንቅ ነው፡፡ አምና የሚገኙት አብዛኛዎቹ ቁልፍ ተጫዋቾች ዘንድሮም በቡድኑ ውስጥ መገኘታቸው በቀላሉ እንዲግባቡ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡

የውድድር ዘመኑን በድል መጀመር

2006 በጥሎ ማለፍ ድል መጀመራቸው ቡድኑን ለሌላ ድል ያነሳሳዋል፡፡ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የዋንጫ ድሎችን ያጣጣሙ ተጫዋቾች በቡድኑ ቢገኙም በመከላካያ የመጀመርያ ድላቸው በመሆኑ ለቡድኑ ህብረት አጋዥ ይሆንላቸዋል፡፡

አጨዋወት

የቡድኑ አጨዋወት ለተጋጣሚ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአብዛኛው 4-4-2 አሰላለፍ ወደሜዳ የሚገቡት አሰልጣኝ ገብረመድህን በአንድ ሆልዲንግ አማካይ እና በአጥቂ አማካይ የሚጠቀሙ ሲሆን ጥላሁን በቀኝ መስመር ቀጥተኛ ጥቃት ይፈፅማል፡፡ ባለ ቀኝ እግሩ ፍሬው ሰለሞን ከግራ በመነሳት ጨዋታ ሲያቀጣጥል ማናዬ ፋንቱ ወደኃላ አፈግፍጎ የፊት አጥቂውን ያግዛል፡፡ ማናዬ ፋንቱ እና ፍሬው ሰለሞን አንድ ቦታ የማይቆሙ በመሆናቸው በተጋጣሚ ቁጥጥር ስር በቀላሉ አይገቡም፡፡ የሁለቱ ተጫዋቾች የመዋለል ብቃት በሜዳ ላይ ቡድኑን የተለያየ ቅርፅ እንዲይዝ ሲያስችል በቀላሉ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል እንዲደርሱ አግዟቸዋል፡፡ በተለይም አሰልጣኙ ለፍሬው ሰለሞን ነፃነት መስጠታቸው ድንቁ አማካይ ወሳኝ ግብ እንዲያስቆጥርላቸው አግዟቸዋል፡፡

ስጋቶች

ትልልቅ ጨዋታዎች

መከላከያ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሁልጊዜም ይፈተናል፡፡ ዘንድሮ በሊጉ እስከ 5 ደረጃ ከያዙት ክለቦች ጋር ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች 1 ሲሸነፍ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል፡፡ ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር የበላይ ቢሆንም ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ለመጨረስ ይሳነዋል፡፡ የክልል ጨዋታዎችም ለመከላከያ አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በቅርቡ በሜዳዎች ጥራት ላይ ምሬታቸውን የገለፁት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው ለሚፈልገው የኳስ ቅጥጥር የበላይነት ጋሬጣ ሆኖባቸዋል፡፡

ተደራራቢ ጨዋታዎች

መከላከያ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክል ሲሆን በርካታ የሲቲ ካፕ ጥሎ ማለፍ እና የሊጉ ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ክለቡ በጥሎማለፉ ወደ ተከታዩ ዙር በማለፉና በሊጉ የክልል ጨዋታዎች የሚጠብቁት እንደመሆኑ ከአፍሪካ ውድድር ተሳትፎው ጋር ተደምሮ አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የደረሰው የውድድሮች ጫና መከላከያን እንዳያዳክመው ያሰጋል፡፡

የስኳድ ጥበት

የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊዎች ድንቅ ቢሆንም መከላከያ ካለበት ተደራራቢ ጨዋታዎች አንፃር በቂ ጥልቀት እና ጥራት ያለው ስብስብ አልያዘም፡፡ ቡድኑ በሁሉም ውድድሮች በተፎካካሪነት ለመዝለቅ በመሃል ተከላካይ በአጥቂ እና በተከላካይ አማካይ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ተጫዋቾች ማስፈረም አለበት፡፡

አጥቂዎች

መከላከያ ዘንድሮ የጣለቸው ነጥቦች በተጋጣሚ ጥንካሬ ላይ የተመሰረተ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ የአጥቂዎች ድክመት ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ 90 ደቂቃ ውስጥ እጅግ በርካታ የግብ እድሎችን የሚፈጥሩት መከላከያዎች ስል አጥቂ በቡድናቸው ቢይዙ ግብ በማስቆጠር የሚደርስባቸው አይኖርም ነበር፡፡ ላለፉት አመታት ግብ አነፍናፊነቱ የሚታወቀው መድህኔ ታደሰ በእድሜ እና ጉዳት የቀድሞ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ ለግብ ማስቆጠር ችግራቸው ዋናው ምክንያት ነው፡፡ በውዝግብ ከኢትዮጵያ ቡና መከላከያን የተቀላቀለው ሙሉአለም ጥላሁንም እድሎችን የመጨረስ ብቃቱ ደካማ መሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡

ማናዬ ፋንቱ ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ ቢሆንም የመጨረስ መሰረታዊ ድክመት አለበት፡፡ በቻን ባመከናት ንፁህ የማግባት እድል በብዙዎች የሚታወቀው ማናዬ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በመስመር እና በመሃል ሜዳ በመሆኑ በባህርዩ ከውስጥ የሚነሳ አጥቂ ነው፡፡ ከውስጥ የሚነሱ አጥቂዎች ከግብ ርቀው ኳስ በመቀበል በክህሎት እና አካል ብቃታቸው ተጠቅመው በፍጥነት ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይገባሉ፡፡ ሚዛናቸውን ስለማይስቱም ግብ ለማስቆጠር አይቸገሩም፡፡ማናዬ ይህን ለመተግበር በአካል ብቃቱ በተለይም ሚዛን አጠባበቅ ላይ ካሻሻለ ምርጥ አጥቂ ይሆናል፡፡

ቀሪዎቹ ጨዋታዎች

መከላከያ ከእረፍት መልስ የሊግ ግጥሚያውን የሚጀምረው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ነው፡፡ ጦሩ በጠንካራ ጨዋታዎች የሚቸገር ቡድን እንደመሆኑ እና ንግድ ባንክ በከፍተኛ መነሳሳት ላይ ያለ እንደመሆኑ ጨዋታው ፈታኝ ይሆንበታል፡፡

11ኛው ሳምንት ወደ ደቡብ አቅንቶ ወላይታ ዲቻን የሚገጥምበት ጨዋታም አስቸጋሪ ጉዞ ነው፡፡ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ያለው ወላይታ ዲቻ ግብ የማስቆጠር ድክመት ካለበት መከላከያ ጋር የሚደረገው ጨዋታ ሶዶ ላይ ከተካሄደ ለጦሩ ለማሸነፍ የሚከብድ ጨዋታ ይሆናል፡፡ በጥሎማለፉ አንደኛ ዙር በሁለቱ መሃከል የተደረገውን ጨዋታ የተመለከተ ሁሉ የዲቻን አስቸጋሪነት ይረዳል፡፡

12ኛው ሳምንት መብራት ኃይልን የሚገጥምበት ጨዋታ ምናልባትም ቀላሉ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መብራት ኃይል ዘንድሮ እጅግ ተዳክሞ እንደመቅረቡ መከላከያ በቀላሉ ያሸንፋል ብለን ብንጠብቅ ምክንያታዊ እንሆናለን፡፡ በዚህ ጨዋታ ለመከላከያ አሳሳቢው ነገር ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለ ወዲህ መብራት ኃይልን አሸንፎ አለማወቁ ነው፡፡ መብራት ኃይል እጅድ በተዳከመባቸው አመታት እንኳን ለመከላከያ እጅ ሰጥቶ አያውቅም፡፡

ጦሩ የውድድር ዘመኑን አንደኛ ዙር የሚያጠናቅቀው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ነው፡፡ ከውዝግቦች በኃላ መከላከያን የተቀላቀለው ሙሉአለም ጥላሁንን ጨምሮ ሲሳይ ደምሴ እና ተስፋዬ በቀለ የቀድሞ ክለባቸውን በሚገጥሙበት ጨዋታ መከላከያ ከአደገኞቹ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡

ግምትአንደኛውን ዙር 5ኛነት ያጠናቅቃል

ቀሪ የመከላከያ ጨዋታዎች

10 ሳምንትየካቲት 2 – ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክበሜዳው

11 ሳምንትየካቲታ 9 – ከወላይታ ዲቻውጪ

12 ሳምንትየካቲት 16 – ከመብራት ኃይልበሜዳው

13ኛው ሳምንትየካቲት 23 – ከኢትዮጵያ ቡናውጪ (አአ)