የቻን ስብስብን ተዋወቋቸው

3ኛ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የሚካሄደው ከሃገር ውስጥ ሊግ ብቻ በተሰባሰቡ ተጫዋቾች የሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) በነገው ዕለት ይጀመራል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር የሚካፈለው የዋልያዎቹ ስብስብን ለመቃኘት ትሞክራለች፡፡


ግብ ጠባቂዎች

ጀማል ጣሰው

እድሜ – 24

ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና

ለብሄራዊ ቡድን ተጫወተ – 12

የ2003 የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋቹ ጀማል የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቀዳሚ ተመራጭ ግብ ጠባቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ድንቅ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ቢሆንም የትኩረት ችግር ይታይበታል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች አስደናቂ ኳሶችን ቢያድንም በትኩረት ማጣት ምክንያት በቀላሉ ግብ ይቆጠርበታል፡፡

ባለፉት 2 ዓመታት ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው የማጣርያ እና የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች በአብዛኛዎቹ ላይ የተሳተፈው ጀማል ቅጣት ወይም ጉዳት ካልገጠመው ቋሚነቱ እርግጥ ይመስላል፡፡ የሲሳይ ባንጫን አለመካተት ተከትሎ ታሪክ እና ደረጄ ለቋሚነት ይፎካከሩታል ተብሎም አይገመትም፡፡ ጀማል ለብሄራዊ ቡድን በርካታ ጊዜያት በመሰለፉ ከሌሎቹ ግብጠባቂዎች አንፃር የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምዱ አለው፡፡


ደረጄ አለሙ

እድሜ – 24

ክለብ – ዳሸን ቢራ

ተጫወተ – 2

ዘንድሮ በሊጉ ብዙም የመጫወት እድል ያላገኘው ደረጄ በክለብ ግልጋሎቱ እምብዛም ባይታወቅም ለብ/ቡድን በርካታ ጊዜያት ተመርጧል፡፡ ያለፉትን አመታት በብሄራዊ ሊግ እንደመቆየቱና ዘንድሮ በአለም ዋንጫ ማጣርያ እና ሴካፋ ዋንጫ ምክንያት በዳሸን ቢራ የመጫወት እድል አለማግነቱ ብዙዎች ብቃቱ ምን እንደሆነ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፡፡


ታሪክ ጌትነት

እድሜ -19

ክለብ – ደደቢት

ተጫወተ – 1

በስብስቡ ውስጥ ከሚገኙት ወጣቱ ተጫዋች ነው፡፡ በደደቢት አምና እና ዘንድሮ ጥቂት የመጫወት እድል ያገኘ ሲሆን የጊዜ አጠባበቁ እና ቅልጥፍናው ጥሩ ጎኑ ነው ፣ በደደቢትም ከሲሳይ ባንጫ ብዙ እንደተማረ መገመት ይቻላል፡፡

ወጣቱ ግብጠባቂ የጨዋታ ልምድ የሌለው በመሆኑ 3ኛ ግብ ጠባቂ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን የተጫወተው 1 ጊዜ ብቻ በሴካፋ ውድድር እንደመሆኑ የትልቅ ውድድር ልምድ የለውም፡፡


ተከላካዮች

አበባው ቡታቆ

እድሜ – 26

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 28 (0)

በስብስቡ ውስጥ ረጅም ዓመት ለብሄራዊ ቡድን በመጫወት የሚበልጡት ደጉ ደበበ እና አዳነ ግርማ ብቻ ናቸው፡፡ ጥሩ የመከላከል ብቃት እና ኳሶችን በረጅሙ የማሻገር ብቃት ይዟል፡፡ የዘንድሮውን ውድድር በዲሲፕሊን ግድፈት ያሳዘነውን ደጋፊ ለመካስ ይጠቀምበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ቢያድግልኝ ኤልያስ

እድሜ – 25

ተጫወተ – 12 (0)

ዘንድሮ ተሸሽለው ከቀረቡ ተከላካዮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሰው በሰው የመያዝ ችሎታው መልካም ሲሆን በእርጋታ ከኋላ ኳስ የመመስረት ችሎታ እና በራስ መተማመንንም ይዟል፡፡


ሳላዲን በርጊቾ

እድሜ – 19

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 7 (2)

የወደፊት የኢትዮጵያ ተስፋ ነው፡፡ የተረጋጋ፣ ጥሩ የኳስ ክህሎት ያለው እና በተክለሰውነቱም ለክፉ የማይሰጥ ነው፡፡ በሴካፋ ዋንጫ ከቶክ ጀምስ ጋር የፈጠረው ጥሩ መግባባት ለብሔራዊ ቡድኑ አዲስ ኃይል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡


ቶክ ጀምስ

እድሜ – 19

ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና

ተጫወተ – 5 (0)

እንደ ሳላዲን በርጊቾ ሁሉ የወደፊት የቡድናችን ተስፋ ነው፡፡ ፈጣን ባይሆንም አጥቂዎችን ለመቆጣጠር አይቸገርም፡፡ በአየር ኳስ በአሸናፊነት የመወጣት ብቃት ያለው ሲሆን ከየትኛውም ተከላካይ ጋር መጣመር ይችላል፡፡


ሥዩም ተስፋዬ

እድሜ -23

ክለብ – ደደቢት

ተጫወተ – 19 (1)

ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ‹የማይነኩ › ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ ሲከላከል ጥሩ ቢሆንም የቦታ አያያዝ እና የአካል ብቃት ችግር ይስተዋልበታል፡፡ ዘንድሮ ከባድ የውድድር ዘመን ጅማሬ እንደማድረጉ ወደአቋሙ እየተመለሰ በሚገኘው አሉላ ግርማ ይፈተናል፡፡


ዓይናለም ኃይሉ

እድሜ – 27

ክለብ – ዳሸን ቢራ

ተጫወተ– 23 (0)

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው እድለ-ቢስ ነበር፡፡ ከናይጄርያ ጋር በተደረጉት የደርሶ-መልስ ጨዋታዎች ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች የተሰጡት በዳሸን ቢራው ተከላካይ ምክንያት ነበር፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ 3ኛ አምበል የሆነው ዓይናለም ቡድን የመምራት እና ከኋላ ኳስ የመጀመር ችሎታ አለው፡፡ የዓይናለም ትልቁ ድክመት ሙሉ 90 ደቂቃ ወጥ ያለመሆን እና ከቡድኑ እንቅስቃሴ የመውጣት ችግር ነው፡፡


ደጉ ደበበ

እድሜ – 29

ተጫወተ – 37 (0)

ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ከጀመረ ዘንድሮ 10ኛ የውድድር ዓመቱን ይዟል፡፡ የቡድኑ አምበል ሲሆን በተሟላ አካል ብቃት ላይ ከተገኘ የቋሚ ተሰላፊነቱ እርግጥ ነው፡፡ ከእድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ ለተደጋጋሚ ጉዳት በመጋለጡና በቦታው ካለው ከፍተኛ ፉክክር አንፃር ይህ ውድድር ለደጉ የመጨረሻ ትልቅ የውድድር መድረክ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


ብርሃኑ ቦጋለ

እድሜ – 27

ክለብ – ደደቢት

ተጫወተ – 22 (1)

የደደቢቱ አምበል በቦታው አበባው ቡታቆ በመኖሩ እድለኛ አይደለም፡፡ ሁልጊዜ የመመረጥ እድል ቢያገኝም የመጀመርያ ተሰላፊነት እድል ማግኘት አልቻለም፡፡ እግር ኳስን በአማካይነት መጀመሩ ጥሩ የኳስ ክህሎት እንዲኖረው አስችሎታል፡፡ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃት እኩል ግልጋሎት ማበርከት የሚችለው ‹‹ፋዲጋ›› ሁለገብነቱ ለቡድኑ ተጨማሪ ኃይል መሆን ይችላል፡፡

አሉላ ግርማ

እድሜ – 20

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ -18 (0)

የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር ተከላካይ በጉዳት በርካታ ጨዋታዎች አምልጠውታል፡፡ ከጉዳት መልስ ጥሩ አቋም ማሳየት ቢችልም አሁንም የተሟላ አካል ብቃት ላይ አይገኝም፡፡ ወደፊት የሚያደርገው ግስጋሴ እና ሸርተቴዎቹ የአሉላ ጥንካሬዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በሚያጠቃበት ወቅት ሰፊ ክፍተት የመተው ድክመት አለበት፡፡


አማካዮች

አስራት መገርሳ

እድሜ– 26

ክለብ – ዳሸን ቢራ

ተጫወተ – 17 (1)

በሜዳ ላይ የማይታየውን ስራ የሚሰራው ረጅሙ አማካይ አሁን በብዙዎች ልብ ውስጥ ገብቷል፡፡ በተለይም በዓለም ዋንጫ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ጎልቶ የወጣ ሲሆን በአሰልጣኙ እምነት ከሚጣልባቸው አማካዮች አንዱ ነው፡፡ ኳስ የመንጠቅ እና የማደራጀት መልካም ችሎታን ይዟል፡፡


አዳነ ግርማ

እድሜ – 28

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 35 (7)

ላለፉት ሁለት ዓመታት ስኬቶች ከግንባር ቀደም ተመስጋኞች አንዱ ነው፡፡ በበርካታ ሚናዎች መጫወት የሚችል እና ቡድን የመምራት ክህሎት ያለው አማካይ/አጥቂ ነው፡፡ በዋልያዎቹ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጥቂነትም ሆነ በአማካይነት በርካታ ጨዋታ በማድረጉ ለአሰልጣኙ ትልቅ አማራጭ ይፈጥራል፡፡


ምንያህል ተሾመ

እድሜ – 28

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 20 (1)

ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተዛወረ በኋላ በአዲስ ሚና መጫወት ጀምሯል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ በግራ መስመር የሚሰለፈው ምንያህል ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰጠውን የ ‹10 ቁጥር› ሚና ጥሩ ግልጋሎት እየሰጠ መሆኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተላመዱትን 4-2-3-1 ለመተግበር ሁነኛ አማራጭ ይሆንላቸዋል፡፡


በኃይሉ አሰፋ

እድሜ – 24

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 16 (1)

የውድድር ዘመኑን በጥሩ አቋም ጀምሯል፡፡ በመስመር ለመጫወትም ትክክለኛው ሰው ነው፡፡ የመስመር ተከላካዮች እንዳይጋለጡ የመሸፈን እና ኳሶችን የማሻገር ብቃት አለው፡፡ አሰልጣኙ በቅርብ ጨዋታዎች እየተጠቀሙበት እንደመሆኑ በቻን ውድድር ላይ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ልንመለከተው እንችላለን፡፡


ምንተስኖት አዳነ

እድሜ – 22

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 4 (0)

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ከሴካፋ ውድድር ከተመረጡ ጥቂት ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ አማካይ በተከላካይ አማካይነት እና በመሃል አማካይነት መጫወት ይችላል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቋሚ ተሰላፊነቱን አለማስከበሩ እና በብሄራዊ ቡድን ብዙ የመጫወት እድል አለማግኘቱ ለቻን ጉዞው ፈተና ይሆንበታል፡፡


ፋሲካ አስፋው

እድሜ – 27

ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና

ተጫወተ – 4 (1)

የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ አሁን አሁን ብዙ የመጫወት እድል ባያገኝም በቋሚነት የብሄራዊ ቡድን ጥሪ እየደረሰው ነው፡፡ በሴካፋ የቡድኑ አምበል እና የሜዳ ላይ መሪ ነበር፡፡ ከጥልቅ የአማካይ ክፍል የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ መምራት፣ በረጅሙ ኳስ የመጣል እና ጥሩ የኳስ ክህሎት አለው፡፡ ለትልቅ ውድድር አዲስ ቢሆንም በርካታ ዓመት የመጫወት ልምድ ስላለው ይቸገራል ተብሎ አይታሰብም፡፡


ኤፍሬምአሻሞ

እድሜ – 22

ክለብ – ኢትዮጵያ ቡና

ተጫወተ– 4 (1)

አምና በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ አጋማሽ የነበረው ድንቅ አቋም አብሮት ባይኖርም አንዳንድ ጊዜ ብልጭ የሚለው ብቃቱን ከደገመ በቻን ጥሩ ጊዜ ሊያሳልፍ ይችላል፡፡ መስመር ላይ ፈጣን እና ጠንካራ ሲሆን ግቦችን ማስቆጠርም ይችላል፡፡


ታደለ መንገሻ

እድሜ – –

ክለብ – ደደቢት

ተጫወተ – 0 (0)

የደደቢቱ አማካይ በመጨረሻ የሚገባውን አግኝቷል፡፡ ታደለ በሊጉ ስታስቲክሶች ባይመዘገቡም በጨዋታ ብዙ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለአጥቂዎች በማድረስ ወደር የለውም፡፡ በክህሎት የበለፀገ አማካይ ነው፡፡ ከመስመር ወይም ከመሃል እየተነሳ አደጋ መፍጠር ይችላል፡፡ በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል ደካማ የሆነው የሰውነት ቢሻው ቡድን ከታደለ መንገሻ የተሻለ አማካይ በቡድኑ ውስጥ ሊያገኝ አይችልም፡፡


አጥቂዎች

ማናዬ ፋንቱ

እድሜ – –

ክለብ – መከላከያ

ተጫወተ – 4 (0)

በሴካፋ ጎልቶ ከወጣ በኃላ በብዙዎች ዓይን ውስጥ ገብቷል፡፡ ካለ ኳስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ለሌሎች የሚፈጥረው የግብ እድል ጠንካራ ጎኖቹ ናቸው፡፡ ማናዬ ትልቁ ድክመቱ ግብ የማስቆጠር ችግር ነው፡፡ ዘንድሮ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው 1 ግብ ብቻ ነው፡፡


ዳዊት ፍቃዱ

እድሜ – 27

ክለብ – ደደቢት

ተጫወተ – 7 (0)

ዘንድሮም በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ ተከላካዮች ከኋላ ኳስ መስርተው እንዳይጫወቱ መጫን እና ከውስጥ አምልጦ ግብ ማስቆጠር ይችልበታል፡፡ የግብ ሪከርዱ አስደናቂ በመሆኑም የአሰልጣኙን ቀልብ ሊገዛ ይችላል፡፡ የጌታነህ ከበደ ክለቡን መልቀቅ ተከትሎ ግብ የማስቆጠር ኃላፊነትን ለብቻው የተሸከመው ዳዊት በብሔራዊ ቡድንም የጌታነህ እና ሳላዲን አለመኖርን የሚጠቀምበት ትክክለኛው ወቅት ላይ ደርሷል፡፡


ኡመድ ኡኩሪ

እድሜ – 23

ክለብ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጫወተ – 16 (4)

በ2013 (2005-06) በቅዱስ ጊዮርጊስ ድንቅ ነበር፡፡ ሊጉን በከፍተኛ ግብ አግቢነት ሲመራ የቅርብ ጊዜ አቋሙ አስፈሪ ነው፡፡ ከየትኛውም ቦታ ግብ ማስቆጠር እና በመስመር አጥቂነት መሰለፍ ይችላል፡፡ በተከታታይ ግብ እያስቆጠረ በመሆኑ በራስ መተማመኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኡመድ ችግር የክለብ አቋሙን በብሔራዊ ቡድን የመድገም ነው፡፡ ከ2010 ወዲህ ለብሄራዊ ቡድን ግብ አስቆጥሮ አለማወቁ ተጫዋቹ በትልልቅ ጨዋታዎች ላይ ያለውን የአዕምሮ ዝግጁነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል፡፡


*ሶከር ኢትዮጵያ