የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ የ1ኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በደደቢት እና ወላይታ ድቻ መሃከል ዛሬ አመሻሽ ተካሂዶ በሰማያዊዎቹ ጦረኞች ፍፁማዊ የበላይነት 4-0 ተጠናቋል፡፡ ጨዋታውከ መጀመሩ አስቀድሞ በሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች እና ስፖርት አፍቃሪያን በጉጉት እንደመጠበቁ የአዲስ አበባ ስታዲየም ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ በተመልካች ተሞልቷል፡፡
ደደቢት በተለመደው 4-2-3-1 (4-5-1) ወደ ሜዳ ሲገባ ታሪኩ ጌትነት ለ5ኛ ተከታታይ ጨዋታ ሲሳይ ባንጫን ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጦ በግብ ጠባቂነት ተሰልፏል፡፡ ወጣቱ ምኞት ዲባባ በመሃልተከላካይነት ሲሰለፍ ታደለ መንገሻ በመሃል አማካይነት ፣ መስፍን ኪዳኔ በአጥቂ አማካይነት ፣ ኄኖክ ኢሳያስ በግራ አማካይነት እንዲሁም ከጉዳት የተመለሰው ዳዊት ፍቃዱ በብቸኛ አጥቂነት ተሰልፈዋል፡፡
በመሳይ ተፈሪ በኩል ከሶስቱ ተከላካዮች አንዱ የሆነው ተክሉ ታፈሰን ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጦ ተስፋዬ መላኩን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ከማካተቱ ውጪ ለውጥ ሳያደርግ በተለመደው 3-5-2 (5-3-2) አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡
በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በባዬ ገዛኸኝ እና ሳምሶን ቆሌቻ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ባለፉት ጨዋታዎች ሳስቶ የታየውን የደደቢት የኋላ ክፍል በቀላሉ መስበር ችለውም ነበር፡፡ በተለይ ባዬ ገዛኸኝ ከዮሴፍ ዴንጌቶ የተሻገሩለትን ኳሶች ወደ ግብ መቀየር ቢችል የጨዋታውን መልክ መቀየር ይችል ነበር፡፡
ደደቢቶች በመስመር በኩል የመስመር ተከላካዮቻቸው እንዳይጋለጡ የወጠኑት እቅድ ሰምሮላቸው የድቻዎችን ፈጣን ሩጫ መግታት ሲችሉ በተቃራኒው ሰማያዊዎቹ መስመሩን በሚገባ ተጠቅመውበት በ34ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን ግብ በመስፍን ኪዳኔ አማካኝነት በግንባር በመግጨት አስቆጥረዋል፡፡ ሶስቱን የድቻ ተከላካዮች በደንብ ተጠግተው ሲያስጨንቁ የነበሩት ደደቢቶች ከተከላካዮች ኳስ በመቀማትና አደጋ በመፍጠር ለድቻዎች አስቸጋሪ ሆነው አምሽተዋል፡፡ 2ኛዋ ግብ በ44ኛው ደቂቃ በድጋሚ በመስፍን ኪዳኔ አማካኝነት የተቆጠረችበት መንገድም የደደቢት አጥቂዎች በድቻ ተከላካዮች ላይ የነበራቸው የቁጥር ብልጫ ውጤትን ያመላከተ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ መሳይ ተፈሪ የደደቢትን የ2-0 መሪነት ለመቀልበስ የመስመር ተከላከዩ አናጋው ባደግን ቀይሮ በማስወጣት ሲስተሙን ወደ 4-3-3 በመቀየር ለማጥቃት ጥረት ቢያደርግም ይባሱኑ የደደቢት የመስመርተከላከዮችን የማጥቃት ነፃነት አጎናፅፏቸዋል፡፡ በተለይም ስዩም ተስፋዬ ቀኝ መስመሩን በሚገባ ተጠቅሞበት ዳዊት ፍቃዱ በ74ኛው ደቂቃ ላስቆጠራት 3ኛ ግብ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ስዩም ከራሱ ሜዳ ጀምሮ እስከ ድቻ ፍፁም ቅጣት ምትክልል ድረስ ከኳስ ጋር ያደረገው ሩጫ አስገራሚ ነበር፡፡ 3ኛዋ ግብ ከተቆጠረች ከ2 ደቂቃ በኋላ የደደቢትን እንቅስቃሴ በጥልቀት ወደ ኋላ አፈግፍጎ በድንቅ ሁኔታ ሲመራ የነበረው ታደለ መንገሻ የማሳረግያውን 4ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
በ2005 በብሄራዊ ሊጉ በ2006 በፕሪሚየር ሊጉ ለተከታታይ 35 ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሰው ወላይታ ድቻ በመጨረሻም ለአምናው ሻምፒዮን ደደቢት እጁን ሰጥቷል፡፡ በ12 ጨዋታዎች በ3 አጋጣሚዎች ብቻ መረቡን ያስደፈረው መክብብ ደገፉም በአንድ ጨዋታ ብቻ 4 ግብ ለማስተናገድ ተገዷል፡፡
ደደቢት የዛሬውን ድል ተከትሎ ነጥቡን ወደ 21 በማሳደግ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ደደቢት በ18 ነጥብ ወደ 5ኛ ወርዷል፡፡
{jcomments on}