መድን አስራት ኃይሌን አሰናበተ

4 ጨዋታ እየቀረው ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ አስራት ሃይሌን ከዋና አሰልጣኝነት አሰናብቷቸዋል፡፡

አሰልጣኙ ዘንድሮ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የክለቡ ቦርድ ለቡድናቸው በቂ እገዛ ባለማድረጉ ወቀሳ ሲያቀርቡ የክለቡ አመራሮች ደግሞ አሰልጣኙ የፈለጓቸውን ተጫዋቾች ማስፈረማቸውን በመጥቀስ ኃላፊነቱን ሊወስዱ እንደሚገባ ሲከራከሩ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከበርካታ ውዝግቦች በኋላ የውጤታማው አሰልጣኝ እና የመድን የ3 አመታት ቆይታ መቋጨቱ ተወርቷል፡፡

በ2004 የውድድር ዘመን ሰማያዊዎቹን በአሰልጣኝነት የተረከቡት አስራት ኃይሌ ቡድኑን በ2005 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከመመለሳቸው በተጨማሪ በሊጉ መልካም የውድድር ዘመን አሳልፈው እየሞተ የነበረውን የአሰልጣኝ ታሪካቸውን ማደስ ችለው ነበር፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የታየው መድን ግን በአሰልጣኙ ታሪክ መጥፎው የሚባል ነው፡፡ ካደረጋቸው 23 የሊግ ጨዋታዎች 1 ብቻ አሸንፎ 10 ነጥቦች ብቻ በመሰብሰብ ሊጉን ተሰናብቷል፡፡

ዘንድሮ በ250 ሺህ ብር የኮንትራት ማራዘምያ ውል የፈፀሙት አስራት ስንብትን ተከትሎ የሁለተኛ ቡድኑ አሰልጣኝ አባይነህ አዲሱ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ይመራሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *