ቻምፒዮኖቹ ሲገመገሙ

2006 አም የፕሪሚየር ሊግ በቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁም የበላይነት የውድድር ዘመኑ ተገባዷል፡፡ ነገ በይፋ ዋንጫውን የሚቀበለው የቻምፒዮኖቹ ስብስብ የውድድር ዘመኑ አቋም ምን ይመስል ነበር ተከታዩ ፅሁፍ የተጫዋቾቹን ብቃት ለመገምገም ይሞክራል፡፡ (-ነጥቦቹ የተሰጡት ከ 10 ነው)

ግብ ጠባቂዎች

ሮበርት ኦዶንግካራ – 7%

ቁመተ መለሎው ግብ ጠባቂ ላይ ግብ ማስቆጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሌሎች የውድድር ዘመናት በተለየ ዘንድሮ ጨዋታዎች በጉዳት ያመለጡት ሮበርት በሊጉ አጥቂዎች ባይፈተንም የተቆጠረበት የግብ መጠንን ከግምት ስናስገባ አሁንም የሊጉ ምርጡ ግብ ጠባቂ መሆኑን እንረዳለን፡፡

ሳምሶን አሰፋ – 5%

በክረምት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተመለሰው ሳምሶን ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ እድል አግኝቷል፡፡ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ብቃት ቢያሳይም ባደረጋቸው ጥቂት ጨዋታዎች እና በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚሰራቸው ስህተቶች ምክንያት ብቃቱን ለመለካት አስቸጋሪ ነው፡፡ ኦዶንግካራ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንደሚለቅ መነገሩ ለሳሚ መልካም ዜና ቢሆንም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 10 አመታት ልምዱ የምንረዳው በሃገር ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ያለው እምነት አነስተኛ ነው፡፡ ወደ ሌሎች ክለቦች ተዛውሮ በመደበኝነት ቢጫወት የብሄራዊ ቡድን ቋሚ ቦታን የማግኘት እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ዘሪሁን ታደለ – 0%

ከ3 አመታት በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የብሄራዊ ቡድኑን በር ለረጅም አመታት በአስተማማኝነት እንደሚጠብቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ዘሪሁን አሁን የቅዱስ ጊዮርጊስ 3ኛ ተመራጭ ግብ ጠባቂ ሆኗል፡፡ ቀደም ብሎ በውሰት መድን በነበረበት ወቅት እና በአንዳንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎች ላይ እንመለከተው የነበረው ዘሪሁን አሁን ቡድኑ ከጨዋታ በፊት ሲያሟሙቅና ከመንፈቅ አንዴ ከሚያገኘው እድል ውጪ ሜዳ ላይ አንመለከተውም፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጥቶ ክህሎቱን የመፈለጊያ ጊዜው አሁን ነው፡፡

ተከላካዮች

2.ቢያድግልኝ ኤልያስ – 7%

በሁሉም የተከላካይ መስመር ቦታዎች በመሰለፍ ከሁሉም ተጫዋቾች በበለጠ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጠቅሟል፡፡ በውድድር ዘመኑ መጀመርያ አካባቢ በመሃል ተከላካይነት ፣ ኋላ ላይ ደግሞ በመስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ቢያድግልኝ ጠንካራ ሸርተቴዎቹ ፣ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ላይ ያለው ብቃት እና ከተጣማሪዎቹ ጋር ያለው መናበብ ጥሩ ነው፡፡ ቢሆንም በመሃል ተከላካይነት ላይ የሚያሳየውን ያህል ብቃት በመስመር ላይ እምብዛም አይደግመውም፡፡ ሲከላከል ጥሩ ቢሆንም በማጥቃቱ ላይ ያለው ተሳትፎ እምብዛም ነው፡፡

3.ሳላዲን በርጊቾ – 7%

ወጣቱ ተከላካይ በቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጥነት ተደላድሏል፡፡ በቡድኑ ውስጥ በርካታ አማራጭ ቢኖርም በቅጣት ካመለጡት እና ከመጀመርዎቹ ጨዋታዎች ውጪ በቋሚ አሰላለፉ የማይታጣ ተጫዋች ነው፡፡ ሳላዲን በዘንድሮው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የጨመረው ትኩስ ጉልበት እና ወጣትነትን ነው፡፡ የደጉ ደበበ አጣማሪ ሲሆን በጉልበት እና ፍጥነት የደጉን ድክመት ለመሸፈን ይጥራል ፤ ከአይዛክ ኢሴንዴ ጋር ሲሰለፍ ደግሞ ወደፊት በነፃነት በመሄድ ለማጥቃት ይሞክራል፡፡ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑ ቢሆንም ሌሎች ተስፈኛ ወጣቶች በቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገጥማቸው አይነት ቶሎ የመላመድ ችግር አልታየበትም፡፡

4.አበባው ቡታቆ – 5%

አበባው በንፅፅር ዘንድሮ የወረደ አቋም አሳይቷል፡፡ በጉዳት እና በማርት ኑይ አፈራርቆ የማጫወት ዘይቤ ምክንያት እንደወትሮው በሁሉምጨዋታ የማናየው አበባው በውድድር አመቱ መጀመርያ ውዝግቦች ውስጥ መግባቱ እና እንደሌሎች የዋልያዎቹ ተሰላፊዎች በብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች መዳከሙ መልካም ላልሆነው የውድድር ዘመኑ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቦታው በርካታ አማራጮች ቢኖሩትም ተፈጥሯዊው የግራ መስመር ተከላካይነትን ከልምድ ጋር ያጣመረው አበባው ብቻ ነው፡፡

5.አይዛክ ኢሴንዴ – 8%

‹‹ ሰራተኛው ›› የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ምርጡ ተከላካይ ነው፡፡ ዩጋንዳዊው ታታሪነትን ፣ ጥብቅነትን ፣ መሪነትን እና ፕሮፌሽናልነትን አጣምሮ የያዘ ተከላካይ ነው፡፡ በመልሶ ማጥቃት የሚመጡ ኳሶችን የመመከት ብቃቱ ዘንድሮ በግልፅ ታይቷል፡፡ አጭር ቢሆንም ከረጃጅም ተከላካዮች ቀድሞ የአየር ላይ ኳሶችን የማጽዳት ችሎታውም ዘንድሮ ዳብሯል፡፡ በቀጣዩ አመት በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያጣው የማይገባ ድንቅ ተከላካይ ነው፡፡

6.አሉላ ግርማ -5%

የአሉላ የዘንድሮ ብቃት ከአበባው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ጉዳቱ አሁንም ተፅእኖ እየፈጠረበት ነው፡፡ ከጉዳቱ ሲመለስ ክብደቱን ጨምሮ ከመሆኑ በተጨማሪ እንደቀድሞው በሙሉ ፍላጎት ጨዋታ ማድረግ ተስኖታል፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኑይ ኃላ ላይ ደግሞ ሬኔ ፌለር ከአሉላ የተሻለ ተነሳሽነት ያለው ቢያድግልኝ ኤልያስን የመረጡትም ለዚህ ይመስላል፡፡

12.ደጉ ደበበ – 6%

ከውድድር ዘመኑ መጀመርያ መጥፎ አጀማመር አገግሞ ወደ አቋሙ ተመልሷል፡፡ በእድሜ መግፋት ምክንያት የአካል ብቃት መውረድ ቢያጋጥመውም ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ ቦታውን አስከብሯል፡፡ በተከላካይ መስመር ላይ ባለው ሁለገብነት የምናውቀው ደጉ ዘንድሮ በተከላካይ አማካይነትም በመሰለፍ ጥሩ ብቃቱን አሳይቶናል፡፡ በብሄራዊ ቡድን አቋሙ ክፉኛ ቢተችም አሁን ባለው ሁኔታ ከደጉ የሚሻሉ ተከላካዮች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡

14. አለማየሁ ሙለታ – 5%

አለማየሁን ጥሩ ተጠባባቂ ብቻ ብለን ልንገልፀው እንችላለን፡፡ ወጣት በመሆኑ ከፊቱ ብሩህ አመታት ቢጠብቁትም ዘንድሮ ቋሚ ተሰላፊ ለማድረግ አሰልጣኞች የሚደፍሩበትን አቋም አላሳየም፡፡ በሁለቱም እግሮቹ መጠቀም መቻሉ ጥሩ ብቃቱ ቢሆንም ገና አልተገራም፡፡ በእንቅስቃሴ መሃል የግራ መስመሩን ትቶ 3ኛ የመሃል ተከላካይ የሚመስልባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡

አማካዮች

7. በኃይሉ አሰፋ – 8%

የዘንድሮ የበኃይሉ አቋም በቅዱስ ጊዮርጊስ ረጅም አመት የቆየ አስመስሎታል፡፡ አምና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲቸገርበት የነበረውን የመስመር አማካዮች እጥረት በሚገባ ቀርፏል፡፡ በኃይሉ ለፈረሰኞቹ ስፋትን ፣ የመስመር ላይ የበላይነትን እና ታታሪነትን አክሏል፡፡ ከመስመር የሚያሸግራቸው ኳሶች እና ተከላካዮችን ወደ መስመር የመለጠጥ ችሎታው ድንቅ ነው፡፡ ኡመድ ኡኩሪ ባይኖር የዘንድሮ የቅዱስ ጊዮርጊስ ኮከብ እሱ ይሆን ነበር፡፡

9.ምንያህል ተሾመ – 5%

የምንያህል የዘንድሮ አቋም አመርቂ አይደለም፡፡ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑ መሆኑ እና አሰልጣኞቹ የሚሰጡት ወጥ ያልሆነ ሚና ይቅርታ እንድናደርግለት ሊያደርግ ይችል ይሆን እንጂ የዘንድሮው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደካማው ተጫዋች ምንያህል ነው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ሜዳ ውስጥ የመደበቅ ፣ የጨዋታ ፍላጎት እና ተነሳሽነት የማጣት ችግሮች የታዩበት ምንያህል አስደሳች ታሪክ ልንለው የምንችለው በ4 የውድድር ዘመናት ከ3 የተለያዩ ክለቦች ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳ የመጀመርያ ተጫዋች ለመሆን መብቃቱ ነው፡፡

10.ዮናታን ብርሃኔ – 0%

እምቅ ችሎታ ያለው ዮናታን ጉዳት የእግርኳስ ህይወቱን እንዳያሰናክለው ያሰጋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናውን ቡድን ሰብሮ ከገባ 4 አመታት ቢቆጠሩም በጉዳት ምክንያት አንድ የውድድር ዘመን መጨረስ ተስኖታል፡፡ ይባስ ብሎ ዘንድሮ ሙሉውን የውድድር አመት ካለ ጨዋታ አሳልፏል፡፡ ዮናታን ዘንድሮ ቢኖር ቀጥተኛ እግርኳስን በሚጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ የሚዋልል እንስቃሴን ያክልበት ነበር፡፡

13. ፍፁም ተፈሪ – 2%

ፍጹም በትልቅ ቡድን ውስጥ የሚቸገር አማካይ ነው፡፡ በሃዋሳ ድንቅ አመታትን አሳልፎ ወደ ደደቢት ቢያመራም ከአስከፊ የውድድር ዘመን በኋላ ወደ ሀዋሳ ተመልሷል፡፡ አምና በንግድ ባንክ እስከ ብሄራዊ ቡድን ምርጫ ያደረሰውን ድንቅ አቋም ቢያሳይም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ በኋላ የደደቢት ጊዜያቱን ማስታወስ ጀምሯል፡፡ በክህሎት የበለፀገ ቢሆንም በሁለት ሆልዲንግ አማካዮች በሚጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቦታ ማግኘት ተስኖታል፡፡ ዘንድሮ ተጫዋቾችን በማፈራረቅ የተጠቀሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁሉም ተጫዋች ተመጣጣኝ እድል እንዲሰጠው ቢያደርጉም ለፍፁም ራሱን የሚያሳይበት እድል በሚገባ አልተሰጠውም፡፡

17. ዊሊያም አሳንጆ – 7%

ጠንካራውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር እንደመጋረጃ የሸፈነው ዊሊያም አሳንጆ ነው፡፡ ጥንካሬው እና ኳስ ለማስጣል እንዲሁም ለማሰራጨት የሚያደርገው ጥረት ድንቅ ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ የውጪ ተጫዋቾች ሁሉ ጠንካራ ሰራተኛ የሆነው ካሜሩናዊ በኳስ ቁጥጥሩ እምብዛም የሆነውን ቡድን የአማካይ ቡድን ሚዛን ለመጠበቅ ከሁሉም አማካዮች በበለጠ እንደመልፋቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያማረ የውድድር ዘመን ተጠቃሽ ሊሆን ይገባዋል፡፡

19. አዳነ ግርማ – 5%

አዳነ ግርማ በአፍሪካ ዋንጫው ካጋጠመው ጉዳት በኋላ የቀድሞውን ታጋይነት ፣ የግብ ማስቆጠር ብቃት እና የአካል ብቃት ማምጣት ተስኖታል፡፡ ዘንድሮ በአመዛኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ቢያደርግም የፈጠረው ተፅእኖ ለ‹‹ምንም›› የቀረበ ነው፡፡ ዘንድሮ በአዳነ ላይ የታየው ትልቁ ድክመት የሚና መለየት ችግር ነው፡፡ እንደ በርካታ ሁለገብ ተጫዋቾች ሁሉ በአንድ ቦታ ላይ ብቃቱን ከማሳደግ ይልቅ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ለመሰለፍ የመሞከሩ ጉዳት አሁን እየታየ ነው፡፡ ወደ ሜዳ የሚገባው በአማካይነት ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው ኳስ ወደሄደችበት አቅጣጫ በመሮጥ ነው፡፡ ቡድኑ በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ በተደጋጋሚ ከመሃል አጥቂው ኡመድ ኡኩሪ ፊት ይገኛል፡፡ ለማጥቃት ወደ ፊት ሲሄድ የሚተወውን ቦታ በፍጥነት ለመድፈን ያለው ተነሳሽነትም ዝቅተኛ ነው፡፡ በአዳነ የዘንድሮ ብቃት ደጋፊውም እራሱም ደስተኛ የሚሆኑ አይመስልም፡፡

21. ተስፋዬ አለባቸው – 3%

በጉዳት አመዛኙን የውድድር ዘመን ካለጨዋታ ያሳለፈው ተስፋዬ ከጉዳት ሲመለስ አቋሙን ለመመለስ እና የቀደመ ቦታውን ለማስከበር ፈተና አጋጥሞታል፡፡ የሀይል አጨዋወትን ከኳስ ማደራጀት ክህሎት ጋር ያጣመረው ‹‹ቆቦ›› ጉዳት ላይ በነበረበት ወቅት የሱን ስራ የሚሰሩ ብዙ አማካዮች መኖራቸው የጊዮርጊስ አስፈላጊው ተጫዋች እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ አሰልጣኞቹ በቶሎ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ያልመለሱትም ለዚህ ይመስላል፡፡

23. ምንተስኖት አዳነ – 7%

መልካም የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡ ከሌሎች አመታት በተለየ በርካታ ጨዋታዎችን በቋሚነት የጀመረው ምንተስኖት በቡድኑ ውጤት ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተፅእኖ መፍጠር ባይችልም በግሉ ምርጡን የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡ ከሁሉም በላይ መብራት ኃይል ላይ ያስቆጠራት የማሸነፍያ ግብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ነጥብ አስገኝታለች፡፡

29. ሳሙኤል አቤይ – 6%

የ ሳሚ ‹‹ሳኑሚ›› የውድድር ዘመን ወጥ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ በመጀመርያ አካባቢ ከቡድኑ ሪትም ጋር ለመጓዝ ሲቸገር አመቱ እየተጋመሰ ሲሄድ ምርጥ ብቃቱን ማውጣት ችሏል፡፡ ወደ መጨረሻ ደግሞ ወርዶ ታይቷል፡፡ የአሰልጣኞች የተለያዩ ፎርሜሽኖች የመሞከር ሰለባ የሆነው ሳኑሚ እውነተኛ የመስመር ተጫዋች መሆኑ በሌሎች ስፍራዎች የመጫወት ብቃቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተ የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡

አጥቂዎች

11. ኡመድ ኡኩሪ – 9%

በቅርብ አመታት ከታዩ አጥቂዎች የኡመድን ያህል በብቃቱ ዙርያ አወዛጋቢ የሆነ ተጫዋች የለም፡፡ አስደናቂ ሩጫው እና ጠንካራ ምቶቹ ቢደነቁለትም እንደ መሃል አጥቂዎች የቦታ አያያዙና ከግብ ጠባቂ ጋር በሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ወደ ግብ የመቀየር ብቃቱ አሳማኝ አይደለም፡፡ የሆነው ሆኖ ዘንድሮ በተለይም በመጀመርያው ግማሽ የውድድር ዘመን ድንቅ ግብ አስቆጣሪነቱን አስመስክሯል፡፡ በእርግጥም ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣዩ አመት ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ወደ ኢትሃድ አሌሳንድሪያ መጓዙን ያረጋገጠው ኡመድን ያጣዋል፡፡

16. ፍፁም ገብረ ማርያም – 8%

ግብ የማስቆጠር ሪኮርዱ አስገራሚ ነው፡፡ በርከታ ጨዋታዎች በጉዳት ቢያልፉትም የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት ደረጃ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የግራ መስመር አጥቂ ሆኖ ቢጫወትም ግብ ከማስቆጠር እና ሚናውን ከመወጣት ያገደው አልነበረም፡፡ በአካል ብቃቱ ላይ ጠንክሮ ከሰራ የብሄራዊ ቡድን አጥቂዎች ደረጃ ላይ መድረሱ የማይቀር ነው፡፡

ይህ እና በዚህ ድረ-ገፅ የሚያነቧቸው ፅሁፎች የሚያንፀባርቁት የፀሃፊውን አቋም ብቻ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *