የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ ፣ አንድ ጨዋታ ደግሞ ነገ ተካሂደው መደበኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ይጠናቀቃል፡፡
ዛሬ በ9 ሰአት ዳሽን ቢራ አርባምንጭ ከነማን በአዲሱ ባህር ዳር ስታድየም ያስተናግዳል፡፡ ዳሽን ቢራ በአዲሱ ስታዲየም የመጨረሻ የሊግ ጨዋታውን እንደሚያደርግ በሳምንቱ አጋማሽ ያሳወቀ ሲሆን ጨዋታው ለባህርዳር ስታዲየም የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መስተንግዶ ይሆናል፡፡ ባህር ዳር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሲደረግባት ከግንቦት 2000 አ.ም. በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ዛሬ በተመሳሳይ 9 ሰአት ሌሎች 4 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ መውረዱን ያረጋገጠው ሐረር ሲቲን ፣ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከነማ ወላይታ ድቻን ፣ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ወራጁ ኢትዮጵያ መድን ሲዳማ ቡናን ሲያስተናግዱ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር መለያየቱ እርግጥ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ ጋር ይፋለማሉ፡፡ ከመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና በመቀጠል ደግሞ ደደቢት ከ መብራት ኃይል ጋር ይጫወታሉ፡፡
እሁድ በሚደረገው ብቸኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተጫውተው የውድድር ዘመኑ መደበኛ መርሃ ግብር ይዘጋል፡፡ (አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢት ከ መከላከያ ይቀራል) ዘንድሮ 5 ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን መሆኑን ቀድሞ ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በእለቱ ዋንጫውን የሚቀበል ሲሆን ዛሬ በሚሌንየም አዳራሽ ድሉን ለማክበር ከደጋፊዎቹ ጋር ቀጠሮ ይዟል፡፡