አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከነገው ወሳኝ ፍልሚያ አስቀድመው መግለጫ ሰጥተዋል

አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከነገው ወሳኝ ፍልሚያ አስቀድመው መግለጫ ሰጥተዋል

ሉሲዎቹ ከዩጋንዳ ጋር ለሚያደርጉት አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ አሰልጣኙ በጨዋታው ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።


የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከዩጋንዳ ጋር ያደረገውን የመጀመርያ ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት ሽንፈት አስተናግደው መመለሳቸው ይታወሳል ፤ አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ በመጀመርያ ጨዋታ እና በመልሱ ጨዋታ ዝግጅት አስመልክቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመጀመርያው ጨዋታ ስለነበው እንቅስቅስቃሴ የተናገሩት አሰልጣኝ ዮሴፍ

“በመጀመርያው ጨዋታ በምንችለው ሁሉ ዘጠናውን ደቂቃ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር። የትኩረት ማጣት እና የልጆቻችን ልምድ ማነስ የተነሳ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረብን ሁለት ጎሎች ተሸንፈን መጥተናል።” ያሉት አሰልጣኙ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ለመቀየር የጨዋታ ዕቅዳቸው ምን እንደሆነ ሲናገሩም

“ በሜዳችን የምንጫወት እንደመሆናችን ከኋላ ኳስን መስርቶ በመውጣት ቶሎ ቶሎ ሰው ሜዳ ለመድረስ ያገኘናቸውን አጋጣሚ ለመጠቀም እንሞክራለን። ምክንያቱም ያለን አማራጭ  መጀመርያ ጎል ማግባት ስላለብን ዓላማችን ሊሆን የሚችለው እርሱ ነው። ወደ ቀጣዮ ዙር ለማለፍ እኔም ልጆቼም የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።”

አስከትለውም በመጀመርያው ጨዋታ የነበረብን ክፍተት ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ ጋር በማያያዝ ሲዘጋጁ እንደነበረ በተለይ የቆሙ ኳሶች ላይ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀው ተጋጣሚያቸው የዮጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጭነው፣ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው እና ረጃጅም ኳሶች ሊጫወቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።