የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዕረፍት መልስ በነገው ዕለት ይጀመራል። የሁለተኛው ዙር መክፈቻ የሆነውን ሐይቆቹ እና ነብሮቹን የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሀዋሳ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕና
የሁለተኛው ዙር ሐይቆቹ እና ነብሮቹ በሚያደርጉት ጨዋታ አሃዱ ብሎ ይጀምራል።
ሊጉ ለሳምንታት ተቋርጦ እንደመምጣቱ ክለቦቹ የሚገኙበትን ወቅታዊ አቋም እያነሱ ሜዳ ላይ ሊኖር ስለሚችለው ጠንካራ እና ደካማ ጎን ማውራት የሚከብድ ቢሆንም ጨዋታው ከመሪው ላለመራቅ ወደ ሜዳ በሚገቡት ነብሮቹ እና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ወሳኝ ድል ማስመዝገብ የሚጠበቅባቸው ሐይቆቹ መካከል እንደመሆኑ ፍልሚያው ተጠባቂ ነው።
ሀዋሳ ከተማ ከአስራ አንድ ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ መቻል ላይ ያስመዘገበው ድል ቢያንስ በወራጅ ቀጠናው ላይ ካሉ ክለቦች በነጥብ እንዲደላደል ቢያስችለውም በመጨረሻው ጨዋታ ግን በንግድ ባንክ ሽንፈት አስተናግዶ ነበር ዙሩን ያገባደደው፤ በነገው ጨዋታ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ግን በመጀመርያው ዙር በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ረገድ የነበሩበትን ደካማ ጎኖች ጠግኖ መግባት ግድ ይለዋል። በተለይም ከወልዋሎ በመቀጠል ጥቂት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ በመጀመርያው ዙር ያስቆጠራቸው ግቦች አስር ብቻ ናቸው። በነገው ጨዋታም ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ እና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነውን ሀዲያ ሆሳዕና እንደመግጠማቸው የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ አድርገው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ካስመዘገቡባቸው መርሐግብሮች በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው የመጀመርያውን ዙር በ2ኛ ደረጃነት ያገባደዱት ነብሮቹ መሪውን እግር በእግር ለመከታተል ዙሩን በድል መጀመር ይኖርባቸዋል።
በመጀመርያው ዙር ከብዙዎች ግምት ውጭ ውጤታማ ጊዜ ያሳለፉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመንፈቁ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የነበራቸው ጥንካሬ ከመሪዎቹ ተርታ እንዲሰለፉ አስችሏቸዋል። በፈጣኖቹ ተጫዋቾች የሚመራው የፊት መስመር አስራ ሰባት ግቦች ማስቆጠር ሲችል
ከመድን እንዲሁም በጣምራ በ2ኛ ደረጃነት ከተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ በመቀጠል ጥቂት ግቦች በማስተናገድ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የተከላካይ ክፍልም የቡድኑ ጠንካራ ጎኖች ናቸው። ነጥብ ከጣለባቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መልስ የቅርብ ተፎካካሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ድል ማድረግ የቻለው የነብሮቹ ስብስብ በነገው ጨዋታ ቀድሞ ድል ማስመዝገብ ከቻለ በመሪው ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀሬ ነው፤ ይህ እንዲሆን ግን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከሚፋለመው ሀዋሳ ከተማ የሚጠብቀው ፈተና በድል መወጣት ግድ ይለዋል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል አማኑኤል ጎበና እና ታፈሰ ሰለሞን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ሌሎች የቡድን አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል በረከት ወንድሙ፣ መለሰ ሚሻሞ እና ጫላ ተሺታ በጉዳት እንዲሁም በኢትዮጵያ ዋንጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው በረከት ወልደዮሐንስ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ክለቦቹ የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሀዋሳ 4 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና 1 አሸንፏል። በቀሪ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 18፣ ሀዲያ ሆሳዕና 14 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።