በተመሳሳይ ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡትን መቐለ 70 እንደርታ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በተመሳሳይ ሃያ ሁለት ነጥብ ሰብስበው በግብ ክፍያ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ከስድስት ሽንፈት አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ያሽቆለቆሉት ምዓም አናብስቱ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ማድረግ ቢያንስ የአንድ ደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል። መቐለ 70 እንደርታዎች በመጀመሪያው ዙር የነበራቸው የመከላከል አደረጃጀት ብርታት የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነበር። ቡድኑ በአምስት ተከታታይ መርሐግብሮች ግብ ሳያስተናግድ ከወጣ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ማስተናገድ ቢችልም እንደ ቡድን የነበረው ውህደት ግን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም፤ ሆኖም አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በቡድናቸው ላይ የታዩት ግለ ሰባዊ የውሳኔ አሰጣጥ ድክመቶች መቅረፍ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ከሚታወቅበት ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ወጣ ባለ መንገድ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የነበረው ቡድኑ በነገው ጨዋታ የተጠቀሰው አወንታዊ ጎን ማስቀጠል ይኖርበታል።
ከተጋጣሚያቸው ተመሳሳይ ሃያ ሁለት ነጥብ በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁለተኛውን ዙር በድል ለመጀመር ምዓም አናብስትን ይገጥማሉ።
በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች ስምንቱን በማሳካት ትልቅ የደረጃ መሻሻል ያገኙት ሀምራዊ ለባሾቹ ዙሩን በጥሩ ብቃት ማጠናቀቃቸው ከወራጅ ቀጠናው እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት ካስተናገደ ወዲህ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሰው ቡድኑ በተለይም በማጥቃቱ ረገድ ጥሩ መሻሻል አሳይቶ ነበር ዙሩን ያጠናቀቀው፤ ቡድኑ ሊጉ ወደ አዳማ ከተማ ከተዘዋወረ በኋላ በተደረጉ የመጀመርያ አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ በማስቆጠር ደካማ አጀማመር ማድረግ ቢችልም ከዛ በኋላ በተከናወኑ አራት መርሐግብሮች ግን ስድስት ግቦች በማስቆጠር ወደ ጥሩ ብቃት መጥቷል። የቅርብ ተፎካካሪው እና በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጥሩ የመከላከል ቁመና ያሳየው መቐለን በሚገጥምበት የነገው ጨዋታም አወንታዊ ጎኖቹን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።
እርግጥ ሊጉ ለሳምንታት ከተቋረጠ በኋላ የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ቡድኖቹ በመጀመሪያው ዙር የነበራቸው ጥንካሬ እና የውህደት ደረጃ ይዘው ለመዝለቅ ሊከብዳቸው ቢችልም ካላቸው የነጥብ መቀራረብ አንጻር በሜዳ ላይ የሚኖረው ፍልሚያ ከፍ እንደሚል ይገመታል።
በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ተመስገን በጅሮንድ፣ ናትናኤል ተኽለ እና ክብሮም አፅብሐ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም ተከላካዩ መናፍ ዐወልም ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም ለጨዋታው ብቁ አይደለም። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ረጅም ጊዜ በጉዳት ላይ የቆየው ሱሌማን ሐሚድ ልምምድ መስራት ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ፉዐድ ፈረጃ በተመሳሳይ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሳተፍም። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ ባዶ ለባዶ አቻ መጠናቀቁ ይታወሳል።