በፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ጠንከር ያለ ቅጣት የተጣለባቸው የአራት ክለቦች 15 ተጫዋቾች የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ ማከናወን ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን አጣርተናል።
ባሳለፍነው ሰኞ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1/2016 በአንቀጽ 7 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በአራት ክለቦች እና በ15 ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ ክለቦቹ የቅድመ ክፍያ (በሦስተኛ ወገን) መክፈላቸውን እና ተጫዋቾቹ መቀበላቸውን አረጋግጫለው በማለት የቅጣት ውሳኔዎችን በክለቦቹ እና በተጫዋቾቹ ላይ ማስተላለፉ ይታወቃል።
ከሰሞኑን በእግርኳሱ ዙሪያ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነውን ጉዳይ በተመለከተ አክሲዮን ማኅበሩ በዛሬው ዕለት ለብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ እንደሚሰጥ ቢጠበቅም ዛሬ በሚጀምረው የ20ኛ ሳምንት ቅጣት የተላለፈባቸው ተጫዋቾች መሰለፍ እንደሚችሉ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ተጫዋቾቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሊጫወቱ የሚችሉበትን ህጋዊ አግባብ ለማጣራት ጥረት ያደረገችው ሶከር ኢትዮጵያ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴው በወሰነው የቅጣት ውሳኔ መሠረት ተጫዋቾቹ ቅጣታቸውን በ7 ቀናት ውስጥ መፈፀም የሚገባቸው ሲሆን ቅጣቱ ከተወሰነ ገና ሦስተኛ ቀን ላይ ስለሚገኝ በቀሪዎቹ አራት ቀናት የተወሰነባቸውን ገንዘብ የሚከፍሉበት ጊዜ ስለሚኖር ዛሬ በሚጀምረው የጨዋታ ሳምንት መጫወት የሚችሉ ይሆናል። ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ ግን አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ ተጫዋቾቹ የተወሰነባቸውን ውሳኔ እስከሚፈፅሙ ድረስ በየትኛውም ጨዋታ ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ ታውቋል። በዚህ አግባብ የቅጣቱ ሰለባ የሆኑት መቻል፣ ሲዳማ ቡና፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማ በዚህኛው ሳምንት ሁሉንም ተጫዋቾች መጠቀም የሚችሉ ቢሆንም የተጣለባቸው የዝውውር እገዳ ግን ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ ታውቋል።