በሙከራዎች ረገድ ፍፁም ደካማ የነበረው የሐይቆቹ እና ነብሮቹ የዙሩ ቀዳሚ ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል።
በፌደራል ዳኛ አባይነህ ሙላት ፊሽካ የጀመረው የዙሩ የመክፈቻ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ለሰላሳ ያህል ደቂቃዎች ቡድኖቹ ለመጫወት የፈለጉትን መንገድ በጉልህ ለመለየት ያልቻልንበት እንዲሁም ረጃጅም ሆነው ይባክኑ የነበሩ ኳሶችን ያስመለከተን ነበር።
ከደካማው እንቅስቃሴ አኳያ በሙከራዎች ረገድ ተዳክሞ በቀጠለው ጨዋታ ሠመረ ሃፍታይ ለሀድያ እስራኤል እሸቱ ደግሞ ለሀዋሳ ዒላማቸውን መጠበቅ ያልቻሉ ሁለት ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ ጨዋታው ወደ መጨረሻቸው አስራ አምስት ደቂቃዎች ሲሻገር ግን መጠነኛ መነቃቃቶችን አሳይቶናል።
31ኛው ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀኝ በኩል ለማጥቃት በሄዱበት ወቅት ሠመረ ከአስቸጋሪ ስፍራ ላይ ሆኖ የሰይድ ሀብታሙን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ መቶ የግብ ዘቡ እንደምንም የያዘበት እና 35ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ ሳጥን ጠርዝ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት አቤኔዘር ዮሐንስ መቶ ሳማኪ ሚካኤል ያዳነበት አጋጣሚ የአጋማሹ ሁለት የተሻሉ ሙከራዎች ሆነው ተመዝግበው አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል።
የተጫዋቾች ለውጥ በሁለቱም በኩል በተመሳሳይ በማድረግ በጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ በሽግግር ለመጫወት ጥረት ያደርጉ የነበሩት ነብሮቹ ለግብ የቀረቡበትን ዕድሎች ፈጥረዋል።
47ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው ክፍል የተገኘን የቅጣት ምት ሔኖክ አርፊጮ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ብረት ከሰይድ ጋር ተጋግዘው ያወጧት እና 64ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የጨዋታ መንገድ እዮብ ከቀኝ ወንድማገኝን አልፎ መሬት ለመሬት መቶ በሰይድ የተያዘችበት ኳስ ቡድኑ ያደረጋቸው ሙከራዎች ሆነዋል።
ተጨማሪ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ጭምር በቅያሪያቸው ለውጠው ካስገቡ በኋላ መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ለመያዝ ጥረትን ያደረጉት ሐይቆቹ በሚያጠቁበት ወቅት በቁጥር አንሰው መገኘታቸው የሀድያን ተከላካዮች አስከፍቶ ሳጥን ውስጥ መገኘት አላስቻላቸውም ለዚህም ማሳያው ሁለቱ ብሩኮች ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎቻቸው ማሳያ ነበሩ በዚህም ደካማ የነበረው መርሃግብር ያለ ግብ ተደምድሟል።