ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለማለት የሚያልመው ሲዳማ ቡና እና በወራጅ ቀጠናው ካሉ ክለቦች ጋር ያለው የነጥብ ልዩነቱ ለማጥበብ ወደ ሜዳ የሚገባው ወልዋሎ የሚያገናኘው ጨዋታ ጠዋት 3:30 ላይ ይደረጋል።

የመጀመሪያውን ዙር በሀያ ሦስት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ይዘው  ያጠናቀቁት ሲዳማ ቡናዎች የሁለተኛው ዙር ጉዟቸው ወልዋሎን በመግጠም ይጀምራሉ።

ሲዳማ ቡናዎች ከብዙዎች ግምት ውጭ በውጣ ውረድ የተሞላ ጉዞ ነበር ያደረጉት፤ ቡድኑ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ መርሐ ግብሮች ከተከታታይ ሽንፈቶች ማገገም ቢችልም ከአቻ ውጤቶች መላቀቅ አልቻለም። ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት የቻለው ቡድኑ በተለይም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ጉልህ ድክመት ነበረው። ጥቂት ግቦች ካስመዘገቡ አራት የሊጉ ቡድኖች አንዱ  የሆነው ሲዳማ ቡና በመጨረሻዎቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው። ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር በተቸገረባቸው አምስት መርሐ-ግብሮች በአራቱ ግብ ሳያስተናገድ በመውጣት ጥሩ የመከላከል ጥንካሬ ማሳየቱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የግብ ማስቆጠር ድክመቱን መቅረፍ ይኖርበታል።

ሰባት ነጥቦች በመሰብሰብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት ወልዋሎዎች በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ለማለምለም ሁለተኛውን ዙር በድል መጀመር ይኖርባቸዋል።

ሰፊ ስራ ለሚጠብቃቸው የሁለተኛ ዙር ውድድር ስንቅ የሚሆን ውጤት ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡት ቢጫዎቹ ጉዟቸው ለማቃናት በርከት ያሉ ለውጦች ማድረግ ግድ ይላቸዋል፤ የመከላከል አደረጃጀቱም አፋጣኝ  መፍትሔ የሚሻ ድክመት ነው።  በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር ቀዳሚ ከሆነው አዳማ ከተማ በመቀጠል ሀያ ሦስት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ መርሐ-ግብሮች ውስን መሻሻሎች ማሳየት ቢችልም የመከላከል አደረጃጀቱ ከዚህም በላይ የማጠናከር ስራ ይጠብቀዋል። ለስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከዘለቀ በኋላ በአራት ጨዋታዎች እራት ግቦች ያስቆጠረው እና በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረው የቡድኑ የማጥቃት ጥምረትም ሌላው መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ክፍል ነው፤ ከተጋጣሚው የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት የመከላከል ጥንካሬ አንፃር በነገው ጨዋታ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም ከወሳኙ መርሐ-ግብር ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ከሌላው ጊዜ በተሻለ ወደ ጨዋታው መቅረብ ግድ ይለዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል ያሬድ ባዬህ ፣ ፍራኦል መንግስቱ እና አበባየሁ ሀጂሶ ወደ ልምምድ ቢመለሱም  ለነገው ጨዋታ አይደርሱም።በወልዋሎ በኩልም ኪሩቤል ወንድሙ በቅጣት ዮናስ ገረመው ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፉም፤ አዲስ ፈራሚው ሳሙኤል ዮሐንስ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

ሲዳማ ቡና አምስት ለባዶ ያሸነፈበት እና የተሰረዘውን የ2012 ጨዋታ ሳያካትት በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና ሦስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ስድስት ግቦች ሲያስቆጥር ወልዋሎ አንድ ማስቆጠር ችሏል።