ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በ20ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት መርሐ ግብሮች መካከል ስሑል ሽረ እና ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በአስራ አምስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ኢትዮጵያ ቡናን ማሸነፍ አንድ ደረጃ እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።

በስድስት መርሐ-ግብሮች አንድ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ ለረጅም ሳምንታት በውጤት መዳከር ውስጥ የቆየው ስሑል ሽረ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ወልዋሎ ላይ ባሳካው ድል
ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር እንዲቀርብ አስችሎታል።  ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ የቀመሰውን ኢትዮጵያ ቡናን በመግጠም የሁለተኛውን ዙር ጉዞውን የሚጀምረው ቡድኑ በመጀመርያው መንፈቅ በሁለቱም ።ፅንፍ በሚገኙ ሳጥኖች የነበረው ደካማ አፈፃፀም መቅረፍ የመጀመርያ ስራው መሆን ይገባዋል። ስሑል ሽረ ምንም እንኳ በጥሩ ብቃት ዓመቱን ቢጀምርም የኋላ ኋላ በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ረገድ የነበሩበትን ጉልህ ድክመቶች ለውጤት መጥፋቱ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

በነገው ዕለትም በመከላከል ጥንካሬያቸው ከፊት ከሚጠቀሱ ክለቦች አንዱ የሆነው እና ጥቂት ግቦች በማስተናገድ በ2ኛ ደረጃነት የተቀመጠውን ቡና እንደ መግጠማቸው የማጥቃት አጨዋወታቸው ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት  ለተጋጣሚዎች ፈተና ያልነበረው የኋላ ክፍል ነገም በቡናማዎቹ ፈጣን አጥቂዎች ጥምረት ብልጫ እንዳይወሰድበት ያሰጋል።

በሀያ ስድስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ዓመቱን ያጋመሰው እና ከመሪው በዘጠኝ ነጥቦች ርቀት የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በነገው ጨዋታ የሚያገኘው ነጥብ መሪዎቹን ይበልጥ ለመቅረብ የሚያግዘው ይሆናል።

ከኳስ ውጭ ባለው ከፍ ያለ ጫና የማሳደር አጨዋወት የሚታወቀው ኢትዮጵያ ቡና እምብዛም ግብ የማይቆጠርበት ዓይነት ቡድን ቢሆንም የማጥቃት አማራጮቹ ተገማች መሆናቸው እና በፊት መስመር ላይ ያለው አባካኘነት በቀላሉ ግቦችን እንዳያገኝ ያደረገው ይመስላል። ፈታኝ ተጋጣሚዎች በገጠሙባቸው የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ መርሐ-ግብሮች ጥሩ ብቃት ያሳዩት ቡናማዎቹ ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር ሲታይ በነገው ዕለት ከባድ የመከላከል ፍልምያ ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ከተጋጣሚያቸው የውጤት አስፈላጊነት አንፃር የሚፈተኑበት ዕድል እንዳለም ይታመናል።

በነገው ጨዋታ ይበልጥ ለሽግግሮች የቀረበ አጨዋወት የሚከተል ቡድን እንደመግጠማቸው ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሰጠ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብለው የሚገመቱት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ጥንቃቄን ሊመርጥ የሚችለውን ተጋጣሚያቸው ለመፈተን የሚያስችል የማጥቃት አጨዋወት ማበጀትም ይኖርባቸዋል።

ስሑል ሽረ በግል ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ከሌለው ነፃነት ገብረመድኅን ውጭ በጉዳትም ይሁን በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ኢትዮጵያ ቡናዎችም በተመሳሳይ ከጉዳትም ይሁን ከቅጣት ነፃ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

ከተሰረዙት የ2012 ዓ.ም ሁለት ጨዋታዎች ውጭ ሦስት ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።ጨዋታዎቹም ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል።