ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ

12፡00 ላይ  ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ የሚያደርጉት ፍልሚያ የተመለከቱ መረጃዎች የመጨረሻው የቅድመ ጨዋታ መረጃዎች ትኩረታችን ነው።

በሀያ አምስት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጀመሪያውን መንፈቅ ያጠናቀቁት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምረው የቀደመው የአሸናፊነት መንገዳቸው ለማስቀጠል አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።

ኤሌክትሪክ ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች በማገገም በድሎች ታጅቦ ነበር የመጀመርያውን ዙር ያገባደደው። በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ወደ ጥሩ ብቃት የመጣው ቡድኑ በአራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን ከማሳካቱም በተጨማሪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው አድናቆት የሚቸረው ነበር። በተለይም በአራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱ ከሌሎች የቡድኑ ጥንካሬዎች የላቀ አፈፃፀም ነበረው። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድናቸው በመጨረሻዎቹ መርሐ-ግብሮች ያሳየው ወጥነት ያለው ብቃት የማስቀጠል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል፤ በነገው ዕለትም በሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስተናገደ ቡድን እንደመግጠማቸው በሊጉ መገባደጃ ጨዋታዎች የተከተሉት ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወታቸው ያስቀጥላሉ ተብሎ ይገመታል።

የመጀመሪያውን ዙር በአስራ ስድስት ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ያገባደዱት አዳማ ከተማዎች ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።

ከአምስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት የመጀመሪያው መንፈቅ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ በውድድር ዓመቱ አስራ አምስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በተለይም በከተማው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ጉልህ የግብ ማስቆጠር ድክመት ተስተውሎበታል።
ቡድኑ ለተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ካለመቻሉም በተጨማሪ በመከላከሉ ረገድ ከሌላው ጊዜ በተለየ አፍሳሽ ሆኗል።

በመጨረሻዎቹ ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አስራ አንድ ግቦች ለማስተናገድ የተገደደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃትም በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ደካማ ጎን ነው፤ በነገው ጨዋታም በጥሩ የማጥቃት ጥንካሬ የመጀመርያውን ዙር ያጠናቀቀው ኤሌክትሪክ እንደመግጠማቸው በዕለቱ የሚኖራቸው የመከላከል ብርታት የጨዋታውን ውጤት ይወስነዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ከአብዱላሂ አላዮ እና ከሱፍቃድ አስረሳኸኝ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ እና ቢኒያም ዐይተን በጉዳት ሙሴ ካቤላ ደግሞ በተመለከታቸው አምስት ቢጫ ካርዶች ምክንያት በቅጣት በነገው ጨዋታ አይኖሩም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ ለ39 ጊዜ ይገናኛሉ። እስካሁን 52 ግቦች ያስቆጠረው አዳማ ከተማ 20 ድሎችን ሲያሳካ አስራ አንድ ጊዜ መርታት የቻለው ኤሌክትሪክ ደግሞ 47 ጎሎች አሉት።