አሜ መሐመድ በሁለቱም አጋማሾች ባስቆጠራቸው ጎሎች አዳማ ከተማ 2ለ0 በሆነ ውጤት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት ሁለተኛውን ዙር በውጤት ጀምሯል።
በፌድራል ዋና ዳኛ ባሪሶ ባላንጎ የመሐል ዳኝነት መመራት የጀመረው የምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ረጃጅም ኳሶች በይበልጥ የጎሉበት ነገር ግን የኤሌክትሪክን የመከላከል ድክመት በመጠቀም የመጨረሻው ሜዳ ላይ ተጠግቶ በመጫወቱ አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ሆነውበታል። በ14ኛው ደቂቃ ኤልያስ ለገሠ በጥሩ ዕይታ በኤሌክትሪክ ተከላካዮች መሐል ለመሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ አሜ መሐመድ በድንቅ ሩጫ ባማረ አጨራረስ እድሪሱ አብዱላሂ መረብ ላይ በማሳረፍ አዳማ ከተማ መሪ እንዲሆን አስችሏል።
ብዙም ብልጫ ለመውሰድ የተደረጉ ጥረቶች ያልነበሩት ቀጣዩቹ ደቂቃዎች በአመዛኙ ወደ መስመር የሚጣሉ ኳሶች የበዙበት ከመሆን በዘለለ በሙከራ ረገድ አይናፋርነት ያጠቃው ነበር። አቤል ሀብታሙ በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃ ውስጥ ከማዕዘን ምት ያገኘውን ኳስ በግንባር ገጭቶ በቀላሉ በናትናኤል ተፈራ ከተያዘበት አጋጣሚ በቀር ደካማ አፈፃፀም የነበራቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተቃራኒው የሜዳ ክፍላቸው ላይም አዳማ ከተማዎች ደጋግመው ያገኟቸውን ዕድል አለመጠቀማቸው እንጂ ተጨማሪ ጎልን ሊያስተናግዱ የሚችሉበት አጋጣሚም እንደነበር መመልከት ተችሏል።
አዳማ ከተማ በሁሉም ረገድ ብልጫውን በወሰደበት ሁለተኛው አጋማሽ እንደነበራቸው ብልጫ ጎል እና መረብን ማገናኘት የቻሉት 55ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከእጅ ውርወራ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ያስጀመረውን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን ሲያሻግር አሜ መሐመድ በግራ እግሩ መቶ በማስቆጠር ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጓል።
በሽግግር ለመጫወት ያደርጉ ከነበረው ውስን ጥረቶች በስተቀር የማጥቃት ደመ ነብሳቸው በእጅጉ ቀዝቃዛ አቀራረብ የነበረው ኤሌክትሪኮች ይባስ ብሎ ደግሞ 60ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ሀብታሙ በሳጥን ውስጥ ተጠልፊያለሁ ቢልም የዕለቱ ዋና ዳኛ ባሪሶ ባላንጎ አስመስለህ ወድቀሀል በሚል በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ከተደረገባቸው በኋላ መበለጣቸው ተባብሶ ቀጥሏል።
ቶሎ ቶሎ ሦስተኛው ሜዳ ላይ ተደራሽ በሆኑ ኳሶች ሙሉ በሙሉ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት አዳማ ከተማዎች በስንታየሁ መንግሥቱ አማካኝነት ሁለት አጋጣሚዎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም መጠቀም ሳይችሉ ቀርው ጨዋታው ተጨማሪ ግቦች ሳናይበት በመጨረሻም በአዳማ ከተማ የ2ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።