ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ድቻ

በመሪነቱ ለመደላደል ወደ ሜዳ የሚገባው መድን እና ወላይታ ድቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች አንዱ ነው።

አስር ድሎች፣ አምስት የአቻ ውጤቶች እና ሁለት ሽንፈቶች በማስመዝገብ ሰላሣ አምስት ነጥቦች ሰብስበው የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ መድኖች ተከታያቸው ሀዲያ ሆሳዕና በትናንትናው ዕለት ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ልዩነቱን ለማስፋት እና በመሪነቱ ለመደላደል ድል ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በሁሉም ረገድ ውጤታማ የመጀመሪያ ዙር ጉዞ ያደረገው መድን በሊጉ ሁለተኛው ብዙ ጎል ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱ እና ጥቂት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬዎቹ ማስቀጠል ከቻለ ለወላይታ ድቻዎች ፈተና መሆኑ አይቀሬ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ ላይ ሦስት ግቦች አስቆጥረው ካሸነፉበት ጨዋታ በፊት በተካሄዱ መርሐግብሮች ተጋጣሚዎቻቸውን በአንድ የግብ ልዩነት ማሸነፍ የቻሉት መድኖች በጨዋታዎቹ እንደፈጠሯቸው ዕድሎች ግቦችን ማስቆጠር አልቻሉም። ቡድኑ በነገው ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ መርሐግብሮች በውጤታማነቱ እንዲቀጥልም የአፈጻጸም ደረጃውን ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።

በአርባምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ከውጤት አልባ ሳምንታት ወደ ጥሩ ብቃት መጥተው በሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች አግኝተው ደረጃቸውን ያሻሻሉት የጦና ንቦቹ ደረጃቸው ለማሻሻል ሙሉ ነጥብ ማግኘትን አልመው ወደ ጨዋታው ይገባሉ። የጦና ንቦቹ አቻ እና ድል ካስመዘገቡባቸው ጨዋታዎች በፊት በተካሄዱ ሦስት መርሐግብሮች በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ ነበር ያደረጉት። ቡድኑ በተጠቀሱት ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስተናግዶ አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር ቢችልም በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ግን መጠነኛ መሻሻል አሳይቶ ነበር ዓመቱን ያጋመሰው። በነገው ጨዋታ ግን ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኝ እና ከተከታዩ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት እያለመ ወደ ሜዳ የሚገባው ኢትዮጵያ መድን እንደመግጠማቸው የሚጠብቃቸው ፍልሚያ ከባድ ነው።

እርግጥ ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ በመካከላቸው የአስራ አንድ ነጥቦች እና ስምንት ደረጃዎች ልዩነት ቢኖርም ከሚመርጡት የተለያየ የአጨዋወት መንገድ አንጻር የነገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 2 ሲያሸነፍ ኢትዮጵያ መድንም በተመሳሳይ 2 አሸንፎ በሦስት አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 9፣ መድን 7 ግቦች በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።