ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አርባምንጭ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አርባምንጭ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በ3ኛ ቀን የ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የሚገናኙት ዐፄዎቹ እና አዞዎቹ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኋላ ሁለት አቻ እና ሽንፈት በማስተናገድ የመጀመሪያውን ዙር መርሐግብራቸውን ያጠናቀቁት አዞዎቹ ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ብሎ ለመፎካከር ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ አስፈላጊያቸው ነው።

በመጀመሪያው ዙር ውጤታማ የፊት መስመር ጥምረት የነበረው አርባምንጭ ከምንም በላይ የመከላከል አደረጃጀቱን ድክመት መቅረፍ አስፈላጊው ነው። በሊጉ ሃያ ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በርከት ያሉ የተከላካይ ክፍሉ ቋሚ ተሰላፊዎች በጉዳት ማጣቱም የኋላ ክፍሉን አሳስቶታል፤ በነገው ጨዋታም በጉዳት ምክንያት የተከላካዮቻቸውን ግልጋሎት የማያገኙት አሰልጣኝ በረከት ደሙ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ስር ነቀል ለውጥ አድርገው የማሻሻል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያው ዙር  ከተገመተው በላይ ውጤታማ የነበረው የፊት መስመሩ ጥምረት ጥንካሬ ማስቀጠልም ሌላው የቡድኑ የቤት ስራ ነው፤  በነገው ዕለት ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ካለው ቡድን ጋር እንደመግጠሙ በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢቸገር እንኳን ከጥቂት አጋጣሚዎች ውጤት ቀያሪ ግቦች ከአጥቂዎቹ ይፈለጋሉ። ከጉዳት መልስ ልምምድ የጀመረው አጥቂው አሕመድ ሑሴንም በአዞዎቹ በኩል የሚጠበቅ ተጫዋች ነው።

በመጀመርያው ዙር አምስት ድል፤ ስምንት አቻ እና አራት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቦ ሃያ ሦስት ነጥቦች የሰበሰበው ፋሲል ከነማ በነገው ዕለት አዞዎቹ ላይ ድል የሚቀናው ከሆነ ቢያንስ ሦስት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አለው።

ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድንን ካሸነፈባቸው መርሐግብሮች በኋላ በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት አስተናግዶ ዓመቱን ያጋመሰው ፋሲል በመጀመርያው ዙር የነበረው የመከላከል ውቅር ዋነኛ ጥንካሬው ነበር። ይህ አወንታዊ ጎናቸውም በሊጉ በማጥቃት ጥንካርያቸው ከሚነሱ የፈጣን መልሶ ማጥቃት ቡድኖች አንዱ የሆነው አርባምንጭ ከተማን በሚገጥሙበት ጨዋታ አንዳች ነገር ይዘው እንዲወጡ ያስችላቸዋል ተብሎ ይገመታል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ከቀደሙት ጊዜያት የተሻለ ውጤታማነት የነበረው የፊት መስመር ጥምረት በመገንባት ሁለት አስፈላጊ ድሎች መቀዳጀት ቢችሉም ቡድናቸው በግብ ዕድሎች ፈጠራ ረገድ አሁንም መሻሻል ይኖርበታል። የተሻለ የአየር ኳስ አጠቃቀም ያለው አዲስ ፈራሚው ቢኒያም ጌታቸውም ለቡድኑ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከረዥም ጊዜ በኋላ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ያገኙት ፋሲሎች ምናልባትም በቋሚ አሰላለፍ ምርጫቸው ላይ ለውጦች አድርገው የሚገቡበት ዕድል እንደሚኖር ይገመታል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ ፣ አበበ ጥላሁን እና አሸናፊ ተገኝ  አሁንም በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።  አህመድ ሁሴን እና ካሌብ በየነ ከጉዳት ተመልሰው ከቡድኑ ጋር ልምምድ የሰሩ ቢሆንም በተለይም የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ አህመድ ሁሴን በቋሚነት ጨዋታው የመጀመሩ ነገር አጠራጣሪ ነው። አሸናፊ ፊዳ በቅጣት አሁንም ጨዋታው ሲያመልጠው ይሁን እንዳሻው ከቅጣት ይመለሳል። እንዲሁም አዲስ ፈራሚዎቹ ፀጋዬ አበራ እና ታምራት ኢያሱ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በፋሲል ከነማ በኩል ከተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ሀቢብ መሐመድ ውጪ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ለነገው ጨዋታ እንደሚቀርቡ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊግ በዘጠኝ አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማ በሦስት አጋጣሚዎች እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች በሁለት አጋጣሚ ሲያሸንፉ የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። በጨዋታዎቹ ዐጼዎቹ 7 አዞዎቹ ደግሞ 5 ግቦች አስቆጥረዋል።