የስፖርት ቤተሰቡ ለመቄዶንያ ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል

የስፖርት ቤተሰቡ ለመቄዶንያ ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል

በሀገራችን እንቁ የእግርኳስ ሰዎች አጋፋሪነት ለመቄዶንያ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ።

የመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ከየካቲት 1 ጀምሮ በሰይፉ በኢቢኤስ እና ሰይፉ ሾ የዩ ቱብ ቻናሎች አማካኝነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት ከ8 ሺ በላይ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ያስጠለለው መቄዶንያ በስሩ የሚገኙ ተረጂዎችን ቁጥር ወደ 20 ሺ ለማሳደግ የሚረዳው ግዙፍ 2 ህንፃዎችን እያስገነባ ሲሆን ለፊኒሺንግ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት አስፈላጊ የሆነውን 5 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ የተጀመረው ንቅናቄ ዛሬ 22ኛ ቀኑን ይዟል።

ባለፉት 22 ቀናት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች እጅግ አስደሳች በሆነ መንገድ እንደየአቅማቸው የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን ይህንን ዘገባ እያዘጋጀን ባለበት ሰዓት በገንዘብ ብቻ ከ582 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል።

ታዲያ በዚህ ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ የተለያዩ የማኅበር ክፍሎች በፊት አውራሪነት ድጋፉ እንዲደረግ ሲያስተባብሩ የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም የስፖርት ቤተሰቡን በተለይ የእግርኳስ ቤተሰቡን ለማስተባበር እንቁ የሀገራችን የእግርኳስ ሰዎች በቀጥታ ስርጭት ድጋፍ እንዲደረግ ሲያስተባብሩ አምሽተዋል። በዚህም ከሀሳቡ አመንጪ ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁን እና ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌ ጋር በመሆን ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፣ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ አዳነ ግርማ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ምንያህል ተሾመ ተቋሙን ጎብኝተው የቀጥታ ስርጭት ስቱዲዮ ተገኝተው ድጋፉን ሲያስተባብሩ ነበር።

በእግርኳስ ሰዎቹ መሪነት በምሽቱ ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የተሰበሰበ መሆኑ ሲገለፅ ከክለቦች የመቻል ስፖርት ክለብ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች 250 ሺ ብር እንዲሁም በቅርቡ የቢ ላይሰንስ ኮርስ የወሰዱት የቀድሞ የዋልያዎቹ ተጫዋቾች እና ኢንስትራክተሮች 70 ሺ ብር በተጨማሪም አዳነ ግርማ በግሉ 100 ሺ ብር ድጋፍ አድርገዋል። የተጫዋቾች ማኅበርም የፊታችን ማክሰኞ በሚኖረው ጠቅላላ ጉባኤ ተጫዋቾችን አስተባብሮ ጠንከር ያለ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ተገብቷል። ከተጠቀሱት ውጪ በርካቶች በተናጥል እና በቡድን ድጋፍ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በቀጣይም መላው የእግርኳስ ቤተሰብ ንቅናቄውን በመቀላቀል ከዚህ በጎ ዓላም ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።

ቴሌብርን ጨምሮ በሁሉም ባንኮች 7979 በመጠቀም ለመቄዶንያ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።