ሪፖርት | የጦና ንቦቹ የሊጉን መሪ አሸንፈዋል

ሪፖርት | የጦና ንቦቹ የሊጉን መሪ አሸንፈዋል

የፀጋዬ ብርሃኑ የመጀመሪያ አጋማሽ ጎል ወላይታ ድቻ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ መድን በሁለተኛው ዙር የመክፈቻ ጨዋታ 1ለ0 እንዲያሸንፍ አስችሎታል።


ተመጣጣኝ በሚመስል እንቅስቃሴ መታጀብ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ ማጥቃትን በመስመር ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች በጊዜ ጎል ያስቆጠሩበት ነበር። በ6ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሀኑ ራሱ ሞክሯት በተከላካዮች ተጨርፋ ወደ ማዕዘን ምትነት የተቀየረች ኳስን ቴዎድሮስ ታፈሠ አሻምቶለት በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ያስቆጠራት ጎል ነበረች ቡድኑን መሪ ማድረግ ያስቻለችው።

በደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች የቆየው ጨዋታ ሊጋመስ አስር ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅት ግን በረጃጅም ኳሶቻቸው ሦስተኛው ሜዳ ብልጫውን ያሳዩት የጦና ንቦች ሁለት ያለቀላቸው ዕድሎች ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም።

37ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የተላከለትን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው አጥብቦ ለማስቆጥረት ሲጥር በአቡበከር ኑራ የዳነበት እና 41ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳርዛ እየነዳ የገባትን ኳስ ኳስ ከግብ ጠባቂው ተገናኝቶ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካዩ በረከት ካሌብ ከጀርባው ደርሶ ያጨናገፈበት ሌላኛዋ ተጠቃሽ ሙከራቸው ነበረች።

መሐመድ አበራ በአንድ አጋጣሚ  ካደረጋት ዒላማዋን መጠበቅ ካልቻለች ኳስ ውጪ በወላይታ ድቻ የሙከራ የበላይነቱ የተያዘባቸው መድኖች ቢኒያም ገነቱን በአጋማሹ መፈተን ሳይችሉ ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በጥሩ ፉክክር የተመለሰው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች ኳስን በመቆጣጠሩ ብልጫውን ቢወስዱም ሦስተኛው ሜዳ ላይ የነበራቸው አፈፃፀም ግን ደካማ ሆኖ የታየበት ሆኗል።

ፈጠን ባለ ሽግግር የሚጣሉ ኳሶችን ተጠቅመው መንቀሳቀስን የመረጡት ወላይታ ድቻዎች 52ኛው ደቂቃ ላይ በዚህ የጨዋታ መነሻ ቴዎድሮስ እና ሙሉቀን ተቀባብለው ሳጥን ይዘው የገቡትን ኳስ ቴዎድሮስ ሞክሮ አቡበከር የያዘባቸው አጋጣሚ በአጋማሹ ቀዳሚዋ ሙከራ መሆን ችላለች።

ብልጫ ቢኖራቸውም ብዙም አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ የማይታዩት መድኖች ዳዊት ተፈራ 76ኛው ደቂቃ እንዲሁም መስፍን ዋሼ በበኩል ወደ ቀኝ ካደላ ስፍራ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ በጥድፊያ ሞክሮ ቢኒያም ከያዘበት ሙከራቸው ውጪ እንደ ነበራቸው ከፍ ያለ ተነሳሽነት ብዙም ዕድሎችን ማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ ጨዋታው በጦና ንቦቹ የ1ለ0 አሸናፊነት ጨዋታው ተቋጭቷል።