ጎል ያስቆጠረላቸውን አጥቂ በቀይ በማጣታቸው ለ75 ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት አርባምንጭ ከተማዎች ፋሲል ከነማን 1ለ0 በመርታት ዙሩን በአሸናፊነት ጀምረዋል።
የምሽቱ ጨዋታ ኳስ እና መረብ የተገናኙበት ገና በ2ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከተከላካይ ጀርባ በሚጥሏቸው ኳሶች ከጅምሩ መንቀሳቀስን መርጠው የተጫወቱት አርባምንጮች መሐል ላይ ያስጀመሩትን ኳስ አህዋብ ብሪያን በንክኪ ያደረሰውን በፍቅር ከተከላካይ ጀርባ ሲጥልለት ከቀናት በፊት ለክለቡ ፊርማውን ያኖረው ታምራት እያሱ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ከግብ ክልሉ ለቆ በመውጣቱ ታግዞ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎልን አስቆጥሯል።
ቀዝቃዛ በነበረው እና ሐይል የቀላቀለበት እንቅስቃሴ በይበልጥ በተንፀባረቀበ ቀጣዮቹ ደቂቃዎች በ15ኛው ደቂቃ ላይ በአርባምንጭ በኩል ጎል አስቆጣሪው ታምራት እያሱን በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ ለማጣት ተገደዋል።
ከፋሲሉ ማርቲን ኪዛ ጋር ኳስን ለመንጠቅ ሲታገል ጥፋት በመፈፀሙ የዕለቱ ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ጎል ሲያስቆጥር ልብሱን በማውልቁ ቀደም ሲል ቢጫ ካርድ መመልከቱን ተከትሎ ለፈፀመው ጥፋት ደግሞ ሁለተኛ ቢጫን በማሳየት ነበር በቀይ ካርድ ሊሰናበት የቻለው።
የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም በተወሰነ መልኩ ኳሱን ወደ ራሳቸው አድርገው መታየት ችለው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች እንደነበራቸው የቁጥር ብልጫ ሳጥን ደርሰው የፈጠሩት ልዩነት ግን አልነበረም።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል የተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ የተመለሱት ዐፄዎቹ ሙሉ በሙሉ ብልጫን ይዘው የታዩ ይምሰል እንጂ ወደ ኋላ በመሳብ ጥቅጥቅ ባለ አደራደር መከላከሉ ላይ ጥብቅ የነበሩትን የአርባምንጭ መከላከልን መስበሩ ተስኗቸው ተመልክተናል።
ኳስን በተዝናኖት በመቀባበል ከመስመሮች በሚነሱ እንቅስቃሴዎች በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይነት እያሳዩ የቀጠሉት ፋሲል ከነማዎች ከነበራቸው ብቻም ሳይሆን የተጫዋች ቁጥርን ብልጫን ጭምር ይዘው ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸው ጎል ማግኘቱ በእጅጉ ሲቸግራቸው የታየ ሲሆን በአጋማሹም የጠራ የግብ አጋጣሚዎች በአንድም አጋጣሚ ሳናስተውል በመጨረሻም ለሰባ አምስት ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች በተጫወቱት የአርባምንጭ ከተማ 1ለዐ አሸናፊነት ተደምድሟል።