በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ለዋንጫ ከታጩ ክለቦች ውስጥ የሆኑት እና በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት ከድል ጋር የተኳረፉ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ድል ካስመዘገቡ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት ብርቱካናማዎቹ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ድላቸው ለማስመዝገብ መቻልን ይገጥማሉ።
በአሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በመጀመርያዎቹ ሳምንት የነበረበትን የውጤት መነቃቃት አሁን ላይ ማስቀጠል እየተሳነው ይመስላል። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ የፊት መስመሩ መዳከም ነው፤ ከድል ጋር በተራራቃባቸው ስምንት መርሐ ግብሮች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር የቀደመው የፊት መስመር ጥንካሬው መመለስ ይኖርበታል። በሀያ ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ተከታታይ ሽንፈት ይዞባቸው ከሚመጣው የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመላቀቅ በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ የማስመዝገብ ግዴታ ውስጥ ሆነው ወደ ጨዋታው ይገባሉ።
በሀያ ሰባት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጀመርያውን ዙር ያጠናቀቁት መቻሎች ከድል ጋር ከተኳረፉ አምስት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል።
ዘለግ ላሉ ሳምንታት ሊጉ መምራት የቻሉት መቻሎች ሊጉ በአዳማ ከተማ መካሄድ ከጀመረ በኋላ በተከታታይ መርሐ-ግብሮች የጣሏቸው ነጥቦች ከመሪው ጋር ያላቸው ልዩነት የዚህን ያህል እንዲሰፋ ምክንያት ሆኗል። በድሬ ቆይታው በአስር ጨዋታዎች ስድስት ድሎች ከማስመዝገቡ በተጨማሪ በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና በግቦች ታጅቦ ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው ቡድኑ በወቅቱ የነበረው ብቃት በቀጣይ ጨዋታዎች መድገም ተስኖታል። የመጀመርያ ዙር ጉዞውን በተከታታይ ሽንፈት ያጠናቀቀው መቻል በአዳማ ቆይታው ማግኘት ከሚገባው ሀያ አንድ ነጥብ ስድስቱን ብቻ በማሳካት ዓመቱን ካጋመሰ በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመምጣት የቀደመው የወጥነት መስመሩን ማግኘት ግድ ይለዋል። ይህ እንዲሆንም በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው የማጥቃት ጥምረት ጥንካሬ መመለስ ይኖርባቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው መሐመድኑር ናስር በጉዳት አይሰለፍም አላዛር መርኔ ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በመቻል በኩል ምንይሉ ወንድሙ እና ሽመልስ በቀለ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ሌሎቹ የቡድን አባላት ግን ለነገው ፍልሚያ ዝግጁ እንደሆኑ ታውቋል።
በሊጉ ከዚህ ቀደም ሀያ ሦስት ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መቻሎች በአስራ ሁለት አጋጣሚ ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ድሬዳዎች ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም የተቀሩት ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።