ፈረሰኞቹን ከጣና ሞገዶቹ የሚያገናኘውን የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብር የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።
ከስምንት ሽንፈት አልባ መርሐግብሮች በኋላ በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግደው ዓመቱን ያጋመሱት ፈረሰኞቹ ከውጤታማው የመጀመሪያ ዙር ጉዞ መልስ ወደ መሪው ይበልጥ ለመጠጋት የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ የጣና ሞገዶቹን ይገጥማሉ። በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቡድኑ ዕድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ይገኛል። በተለይም ሊጉ በአዳማ ከተማ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ ወደ ጥሩ ብቃት መጥቷል። በመጨረሻዎቹ መርሐግብሮች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ከመያዝ በዘለለ በማጥቃቱ ረገድ በጎ ለውጦች ያመጣው ቡድኑ ከመቻል እና መድን በመቀጠል ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ የፊት መስመር አለው። ከመድን ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስተናገደውን ባህር ዳር ከተማ በሚገጥሙበት ጨዋታ ከባድ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ቢገመትም ከነገው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ለቀጣይ ጉዟቸው ወሳኝ እንደመሆኑ በልዩ ትኩረት ወደ ጨዋታ ይቀርባሉ ተብሎ ይገመታል።
ሀዋሳ ከተማን ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ አቻ እና ሁለት ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ፋሲል ከነማ ላይ የ2ለ1 ድል በመቀዳጀት ነበር የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት። ሆኖም በዚህ ጨዋታ ላይ የነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ግን በመሃል ከሀላባ ከተማ ጋር ባደረጉት የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ መቀጥል አልቻለም ነበር። በመደበኛው ደቂቃ ያለግብ ተለያይተው በመለያ ምት ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያስገደዳቸው ደካማ የነበረው የማጥቃት ኃይል እጅግ የነጥብ መጠጋጋቶች ባሉበት ፕሪሚየር ሊጉ ላይ እንዳይቀጥል የአሰልጣኘ ደግአረገ ይግዛው የመጀመሪያው የቤት ሥራ ነው። ከኢትዮጵያ መድን (6) ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ቡና እኩል ዝቅተኛውን የግብ መጠን (11) ያስተናገዱት ባህር ዳር ከተማዎች ይህን እጅግ የሚተማመኑበት ክፍል ጥንካሬ ካስቀጠሉ ለነገው ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈተና መሆናቸው አይቀርም። የሊጉ መሪ መድን ዛሬ በድቻ መሸነፉን ተከትሎ ነገ ካሸነፉ ፐልዩነቱን ወደ 6 የማጥበብ ዕድሉ ያላቸው የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ የሚያስመዘግቡት ውጤት በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የሚጠብቋቸው እጅግ ወሳኝ መርሐግብሮች ላይ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጉዳት ላይ ሆኖ የቆየው በረከት ወልዴ ወደ ሜዳ ሲመለስ እንዲሁም የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ዝግጁ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በኩልም ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ አምስት ቢጫ ላይ የነበረው መሳይ አገኘሁም ቅጣቱን በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ጨርሷል።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 11 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ሦስት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት ድሎችን አሳክተው ስድስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ አስር ባህር ዳር ከተማ ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥረዋል።