ባህርዳር ከተማዎች በወንድወሰን በለጠ ሦስት ጎሎች ታግዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የ4ለ1 ድል ተቀዳጅተዋል።
ሳምንቱን የሚያሳርገው እና በኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ የተመራው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በተለይ የመጀመሪያውን አስራ አምስት ደቂቃ ብልጫውን የወሰዱት ፈረሰኞቹ ቀዳሚ የሆኑበት ጎል አግኝተዋል። ሻሂዱ ሙስጠፋ ካደረጋት ሙከራ በኋላ 14ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ወደ ግራ የተለጠጠ ኳስን ያገኘው ቢኒያም ፍቅሬ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ክልል ሲያሻግር የግብ ጠባቂው ፔፕ ሰይዶ የቦታ አያያዝ ስህተት ታክሎበት ተገኑ ተሾመ ጎል አድርጓት ቡድኑን መሪ አድርጓል።
በመፈራረቅ በጨዋታው ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ባሻገር ባህር ዳሮች በይበልጥ እየተሻሻሉ በመጡበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ቡድኑ 28ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ለግብ ተቃርቦ ነበር። ከማዕዘን መነሻዋን ያደረገች ኳስን የግቡ ሳጥን ጠርዝ ያገኘው ፍጹም ዓለሙ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የሞከራትን አጋጣሚ ባሕሩ ነጋሽ እንደምንም ወደ ውጪ አውጥቶበታል።
ወደ ጨዋታ የምትመልሳቸውን ጎል ለማስቆጠር በይበልጥ ለሳጥኑ የተጠጋውን እንቅስቃሴ ያዘወተሩት ባህርዳሮች 39ኛው ደቂቃ ላይ በግሞት ከሃያ አምስት ሜትር ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት መሳይ አገኘሁ በቀጥታ መቶ በማስቆጠር ቡድኑን 1ለ1 አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ተመልሶ ሁለቱም ቡድኖች መሪ ለመሆን ፈጣን ሽግግር በዋናነት ተጠቅመዋል። ከነዚህም መካከል 50ኛው ደቂቃ ላይ በባህር ዳር ከተማ በኩል ቸርነት ጉግሳ በሳጥኑ የግራ ክፍል በግሩም ሁኔታ ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻግሮት ወንድወሰን በለጠ ኃይል በሌለው ሙከራ ሲያበክነው በሰከንዶች ልዩነት ደግሞ በፈረሰኞቹ በኩል ብሩክ ታረቀኝ ከቅጣት ምት በረጅሙ አሻግሮ ከጥቂት ንክኪ በኋላ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ያደረገው ጥሩ ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣበት ሙከራ ልዩነት ፈጣሪ የሆነች ግብ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ከመቆጠሯ በፊት ለግብ የቀረቡ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በጨዋታው የበላይ እየሆኑ የመጡት እና የተቃራኒን የግብ ክልል ደጋግመው ሲጎበኙ የነበሩት ባህርዳሮች 61ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ ወንድወሰን በለጠ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪነቱን እንዲረከቡ አስችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ፈረሰኞቹ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቶሎ ቶሎ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ቢደርሱም ዒላማውን የጠበቀ የጠራ ሙከራን ግን አላስመለከቱንም ፣ ይልቁንም የጣና ሞገዶች በመልሶ ማጥቃት የፈረሰኞቹን ተከላካይ መስመር መፈተናቸውን ቀጥለዋል።
66ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ ወንድወሰን በለጠ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ከግቡ ቋሚ ብረት ለጥቂት ወጥቶበታል። 76ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል ያገኘውን ኳስ ወንድወሰን በለጠ አግኝቶ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና ቀድሞ የተቆጣጠረበት ሌላኛው አስቆጪ አጋጣሚ ይጠቀሳል።
የጎል የበላይነት የወሰዱት ባህርዳር ከተማዎች ሳይጠበቅ ሁለት ግቦችን አከታትለው አስቆጥረዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬዘር ካሣ ከመሃል ሜዳ አካባቢ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ በተከላካይ ከተጨረፈ በኋላ ወንድወሰን በለጠ በብልሃት ደርሶ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ መሪነታቸውን ማጠናከር ሲችል የሦስተኛው ጎል መቆጠር የረበሻቸው ፈረሰኞቹ ከአንድ ደቂቃ በኋላ አራተኛውን ግብ አስተናግደዋል።
በ85ኛው ደቂቃ ፍጹም ዓለሙ ከተከላካይ ጀርባ መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ወንድወሰን በለጠ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ደርሶ ወደ ግብነት ቀይሮ ለሞገዶቹ መሪነታቸው ወደ አራት ከፍ አድርጎ በሰፊ ግብ ልዩነት ጨዋታውን አሸንፈው እንዲወጡ አስችሏቸዋል።