በቼክ ሪፓብሊክ ቆይታ የነበረው አጥቂ ወደ ቢጫዎች ለማምራት ከጫፍ ደርሷል።
ቀደም ብለው የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ዮሐንስ እና አማካዩ ሀብታሙ ንጉሴን ለማስፈረም ከስምምነት የደረሱት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር ዩጋንዳዊውን አጥቂ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል።
ቡድኑን ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ፉሃድ አዚዝ ባዮ ነው ፤ በሀገሩ ክለብ ፕሮላይን የእግርኳስ ሂወቱን ጀምሮ በዛምብያው ብዩልድ ኮን፣ በዩጋንዳው ቫይፐርስ ፣ በእስራኤሎቹ አሽዶድ እና ቤኒ ሳክኒን ከተጫወተ በኋላ በቼክ ሪፐብሊክ ሁለተኛ የሊግ እርከን ‘ Chance Narodni Liga’ ተሳታፊ በሆነው ‘ኤም ኤፍ ኬ ቪስኮቭ’ ሲጫወት የቆየው አጥቂው በአውሮፓው ክለብ የነበረው ቆይታ አጠናቆ ማረፍያው የቢጫዎቹ ቤት ለመሆን ተቃርቧል።
በፊት አጥቂነት እንዲሁም በመስመር አጥቂነት መጫወት የሚችለው እና በዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን መለያ በሀያ ስምንት ጨዋታዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለው ፉሃድ አዚዝ ባዬ ቀደም ብሎ ከራዮን ስፖርት እና ያንጋ አፍሪካ ጋር ስሙ በስፋት ሲያያዝ ቢቆይም ማረፍያው ወልዋሎ ለማድረግ በቀጣይ ቀናት የወረቀት ጉዳዮች አጠናቆ በይፋ የቡድኑን ተጫዋች ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።