የ21ኛው ሳምንት የመዲናይቱ አንጋፋ ክለቦች በሚያገናኘው ጨዋታ ይጀመራል።
ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ ዓመቱን ካጋመሰ በኋላ ሁለተኛውን ዙር በሽንፈት የጀመረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዳማ ከተማው ሽንፈት ቶሎ ለማገገም በአራት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጠውን ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማል።
የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ኤሌክትሪክ በተለይም በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ እንዲሁም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎቹ አፈፃፀም ይበል የሚያሰኝ ነበር። በአዳማ ከተማ ሁለት ለባዶ በተሸነፈበት የመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ግን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ የነበረው ደካማ ብቃት ለሽንፈት ዳርጎለታል። ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ በዕለቱ በነበራቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልሆኑ ያልሸሸጉት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ተጋጣሚ መረብ ላይ ያሳረፈው እና በአዳማው ጨዋታ ውጤታማ ያልነበረው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማስተካከል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል። ቡድኑ በነገው ዕለት ለተከታታይ ሦስት መርሐ-ግብሮች መረቡን ሳያስደፍር የዘለቀውን የቡናማዎቹ የኋላ ክፍል በምን መንገድ ይፈትናል የሚለውም ተጠባቂ ነው።
በኮንኮኒ ሃፊዝ ብቸኛ ግብ ስሑል ሽረን በማሸነፍ የሁለተኛው ዙር ጉዟቸው አሀዱ ብለው የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸው ሀያ ዘጠኝ በማድረስ በ4ኛ ደረጃነት ተሰይመዋል።
ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣው እና በሊጉ ሁለተኛው ጥቂት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በጥንካሬው መዝለቁ በቡናማዎቹ በኩል ከሚነሱ አወንታዊ ነጥቦች አንዱ ነው። እንደባለፈው ዓመት ዘንድሮም ጠንካራ የመከላከል ውቅር ያለው እና ከኳስ ውጭ ታታሪ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በያዙት የድል መንገድ ለመዝለቅ በቅርብ ሳምንታት ውስን መቀዛቀዞች ላሳየው የፊት መስመራቸው ግብ የማስቆጠር ድክመት አወንታዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
እርግጥ ቡድኑ ጠንካራ ተፋላሚዎች ከሆኑት መቻል፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ ጋር ባደረገቸው ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች ይዞ መውጣቱ የሚያስወድሰው ቢሆንም ጨዋታዎችን በጠባብ ውጤት ከማገባደድ አባዜው መላቀቅ ይኖርበታል። ከመጨረሻዎቹ አምስት ድሎቹ አራቱ በአንድ ለባዶ ጠባብ ውጤት የፈፀመው ቡና በቀጣይ ውጤት ለማስጠበቅ ከሚመጣው ጫና ለመላቀቅ የግብ ማስቆጠር ብቃቱ ከዚህም በላይ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።
በኢትዮ ኤሌትሪክ በኩል በአዳማው ጨዋታ ወቅት ጉዳት ካስተናገዱት ሦስቱ ተከላካይ መካከል ጌቱ ባፋ እና ዲንግ ኪያር ከጉዳታቸው አገግመው ለነገው ጨዋታ ሲደርሱ አብዱላዚዝ አማን ግን ለሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ሲጠበቅ አቤል ሀብታሙ በቅጣት የማይኖር ሲሆን እንዲሁም ጉዳት ላይ የሚገኘው አብዱላሂ አላዮ አሁንም ከስብስቡ ውጭ መሆኑ ታውቋል። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ የሚደርሱ ይሆናል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም የቡድኑ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ43 ጊዜያት ተገናኝተው ቡና 23 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት እዟል። 10 ጨዋታ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፍ 10 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 73 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ 45 አስቆጥሯል።