ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ሀድያ ሆሳዕና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ ሀድያ ሆሳዕና

ሁለተኛውን ዙር በአቻ ውጤት የጀመሩት ቡድኖች የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ነው።

ከወልዋሎ ጋር ነጥብ በመጋራት የመጀመርያውን ዙር ጉዟቸው የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በሀያ አራት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሲዳማ ቡናዎች አሁንም የግብ ማስቆጠር ችግራቸው ባለመቅረፋቸው ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ አልቻሉም። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በአወንታዊ ጎን የሚነሳለት ጥሩ የመከላከል ጥንካሬ መላበስ ቢችልም ለግብ ማስቆጠር ችግሩ መፍትሔ ማበጀት አልቻለም። በመጨረሻዎቹ ስድስት መርሐ-ግብሮች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘት የቻለው ቡድኑ የተጠቀሰው የፊት መስመር ድክመቱ  ውጤት በአቻ ውጤቶች እንዲታጀብ አድርጎታል።
በአዳማ ከተማ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ አምስቱ በነጥብ መጋራት የፈፀመው ሲዳማ ቡና በቀጣይ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ ቀዳሚ የቤት ስራው መሆን ይገባዋል።

አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ለወጣው የነብሮቹ የመከላከል አደረጃጀት የሚመጥን የማጥቃር አጨዋወት ከማበጀት ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻል ያሳየው የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬ የማስቀጠል ስራም ይጠብቃቸዋል።

ነብሮቹ በሁለተኛው ዙር መክፈቻ ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው መውጣት ቢችሉም መሪው መድን ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አራት ዝቅ ማድረግ ችለዋል። 

ቡድኑ ምንም እንኳን በመጨረሻው ጨዋታ ከሀይቆቹ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም በጨዋታው የነበረው እንቅስቃሴ ለክፉ የሚሰጥ አይደለም። ሲዳማ ቡናዎች በሙከራዎች ባልደመቀው ጨዋታ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ባይካድም የቡድኑ የማጥቃት ጥንካሬ ግን በወትሮው አቋሙ አልነበረም። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጨዋታው ከዚህ ቀደም የነበሩባቸው ጥንካሬዎች ለማስቀጠል የተሻሉ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው አመለካች መሆኑን በመጥቀስ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ግብ ለማስቆጠር ምቹ ሁኔታዎች አለመፍጠሩ የገለፁት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በቀጣይ በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ለውጦች እንደሚያደርጉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ቡድኑ ሦስት ግቦች ካስተናገደበት ጨዋታ መልስ ወደ ቀደመው የመከላከል ጥንካሬው ተመልሶ በተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን አለማስደፈሩ እንዲሁም በስብስቡ ውስጥ ያለው ፍላጎት እና ትጋት አሁንም በዋንጫ ፉክክሩ እንደሚዘልቅ ማሳያዎች ቢሆኑም በቅርቡ ወደ መልካም የመከላከል ጥንካሬው የተመለሰው ሲዳማ ቡና በሚገጥሙበት የነገው ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ላይ በተሻለ የማጥቃት ጥንካሬ መቅረብ ግድ ይላቸዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል ያሬድ ባዬ፣ አበባየሁ ሀጂሶ፣  ደስታ ዮሐንስ ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ፍራኦል መንግስቱ ያለፉትን ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ቡድናቸውን እያገለገሉ አለመሆናቸው ሲታወቅ ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገርም አሁንም  አጠራጣሪ ነው።በሀድያ ሆሳዕና በኩል በረከት ወልደ ዮሐንስ ከቅጣት ሲመለስ ጫላ ተሺታ ለሳምንታት ከሚዳ የሚርቅ ሲሆን መለሰ ሚሻሞ፣ በረከት ወንድሙ እና ዳግም ንጉሴ አሁንም ለነው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ቃልአብ ውብሸት በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። ሌሎቹ የነብሮቹ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተሰምቷል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 11 ጨዋታዎች አድርገዋል። ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 19 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና አምስት ፣ 12 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡናም ሦስት ድሎችን አስመዝግበዋል