የኢትዮጵያ ሴቶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ተጋጣሚ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውና አሸንፋለች።
ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣርያ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ መከናወን የሚጀምሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በዙሩ ከካሜሩን አቻው ጋር ተደልድሏል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ራውዳ ዓሊ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከየካቲት 14 ጀምሮ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።
ተጋጣሚያችን ካሜሩን በመጀመሪያው ዙር የግብፅ አቻዋን በድምር ውጤት 6ለ0 አሸንፋ የኢትዮጵያን ፍልሚያ እየተጠባበቀች ሲሆን የቡድኑ አሠልጣኝ ንዶኮ ጆሴፍ ብሪያን የካቲት 7 ለ30 ተጫዋቾች (ሦስት ግብ ጠባቂዎች፣ አስር ተከላካዮች፣ ሰባት አማካዮች እና አስር አጥቂዎች) ጥሪ አቅርበው ዝግጅታቸውን ያውንዴ በሚገኘው ካፍ የልህቀት ማዕከል እያከናወኑ ይገኛሉ።
ጠንከር ያለ ዝግጅቱን እየሰራ የሚገኘው ቡድኑ በትናንትናው ዕለት በኦሌምቤ ስታዲየም ከኤስ ኤ ኤ ላይትኒንግ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ ሁለት ለምንም አሸንፏል። በጨዋታውም በጊኒ ሱፐር ሊግ ተስፈኛ ተብላ የተመረጠችው አጥቂዋ ቲዋ ሊሲ ፍራቼ ሁለቱንም ጎሎች ከመረብ አሳርፋለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን የፊታችን ቅዳሜ ከሜዳው ውጪ የሚያከናውን ይሆናል።