ኮንኮኒ ሀፊዝ ከቀናቶች በኋላም ያስቆጠረው ጎል ኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 በሆነ ውጤት ኢትዮ ኤሌክትሪክን እንዲረታ አስችሎታል።
ሁለተኛውን ዙር በአዳማ ሽንፈት በማስተናገድ የጀመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአራት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን ሲያደርጉ ጌታሁን ባፋ ፣ አብዱላዚዝ አማን ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና አቤል ሀብታሙን በሚኪያስ ካሳሁን ፣ በጋሻው ክንዴ ፣ ሔኖክ ገብረህይወት እና ፍቃዱ ዓለሙ ሲተኩ በስሑል ሽረ ላይ ድልን የተቀናጁት ኢትዮጵያ ቡናዎች ምንም ቅያሪን ሳያደርጉ ገብተዋል።
የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክርን ያሳየን ቢመስልም ፈጠን ባሉ ሽግግሮች በጥልቅ ለመጫወት የጣሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሙሉ በሙሉ ብልጫውን የወሰዱበት ነበር። ቡድኑ መሐል ሜዳውን በይበልጥ በመለጠጥ ከመስመር ወደ ውስጥ ተስበው መንቀሳቀስን በጀመሩበት ቅፅበት 18ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኩ አማካይ ሀብታሙ ሸዋለም የተሳሳተውን ኳስ ያገኘው ይታገሱ ታሪኩ በጥሩ ዕይታ አመቻችቶለት ኮንኮኒ ሀፊዝ በድንቅ አጨራረስ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ጎልን አስቆጥረው ቀዳሚ ከሆኑባት ደቂቃ አንስቶ በይበልጥ ለሳጥን በመጠጋት ለኤሌክትሪክ ተከላካዮች ራስ ምታት መሆናቸውን የቀጠሉት ቡናማዎች በአማኑኤል አድማሱ እና ዲቫይን ዋቹኩዋ አማካኝነት ተጨማሪ ጥራት ያላቸውን ሙከራዎችም ሰንዝረዋል። በተጋጣሚያቸው በተወሰደባቸው ብልጫ የመጫወቻ ቦታን ለማጣት የተገደዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በድግግሞሽ ጫና ውስጥ ለመግባት ተገደዋል።
31ኛው ደቂቃ ሚኪያስ በመከላከል የሰራውን ስህተት ያስተዋለው አማኑኤል ወደ ውስጥ ጠልቆ ገብቶ ያሻገረውን ኮንኮኒ ነክቶ ያመቻቸለትን ዲቫይን ቢመታውም ኢድሪሱ አብዱላሂ ሲያወጣት 38ኛው ደቂቃም ዲቫይን ከርቀት መቶ አግዳሚ ብረቱ ያወጣበት እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ከግራ ወደ ሳጥን በጥሩ የእግር ስራ ያሻገረው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ በግብ ዘቡ ሲመለስ ዳግም ኮንኮኒ ሞክሮ ኢድሪሱ አብዱላሂ የያዛት ኳስ የቡናማዎቹን የበላይነት የሚያሳዩ ጠንካራ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ቡናማዎቹ ከቆሙበት የእንቅስቃሴ የበላይነታቸው ለሀያ ደቂቃዎች ያህል ወስደው የቆዩበት ነበር። በ51ኛው ደቂቃ ከቀኝ በኩል ከቅጣት ምት ዲቫይን ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ ወደ ግብ ሞክሯት ግብ ጠባቂው እድሪሱ አብዱላሂ አጋጣሚዋን ካመከናት ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ብቻውን ሳጥን ውስጥ ኮንኮኒ በደረት ያቀዘቀዘውን ኳስ ወደ ውጪ የሰደደበት አጋጣሚም የቡድኑ ጠጣሮቹ ዕድሎች ሆነዋል።
የተጫዋች ቅያሪን ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ በማድረግ በይበልጥ ወደ እንቅስቃሴ በመግባት ወደ ሳጥን ደጋግመው ኤሌክትሪኮች የደረሱ ቢሆንም በጨዋታው ላይ ከነበረው ቀዝቃዛ የፉክክር እንቅስቃሴ በቀር በሙከራዎች መታጀብ የተሳነው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና የ1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።