ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከ21ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት መርሐ ግብሮች መካከል በሁለት የተለየ የውጤት ጎዳና በመጓዝ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኛው ጨዋታ ረፋድ 3:30 ይጀመራል።

ከስድስት ተከታታይ ድል አልባ መርሐግብሮች በኋላ ወልዋሎን አሸንፈው የመጀመሪያውን ዙር ያገባደዱት ስሑል ሽረዎች በሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ቻምፒየኖቹን ይገጥማሉ።

በመከላከሉ ረገድ በቀላሉ ተጋላጭ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየታየ የሚገኘው ሽረ እንደ ቡድን ከኳስ ውጭ በተደራጀ መልኩ ከመከላከል አንፃር ወስንነቶች አሉበት፤ ቡድኑ ከመቻል እና መድን ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች በድምሩ አምስት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ ባከናወናቸው መርሐ ግብሮች በጨዋታ ከአንድ በላይ ሳያስተናግድ በመውጣት የሚቆጠሩበትን ግቦች መቀነስ ቢችልም የኋላ ክፍሉ አሁንም መሻሻሎችን ይፈልጋል። የማጥቃት አጨዋወቱን ማስተካከል ሌላው በስሑል ሽረዎች በኩል የሚጠበቅ ነገር ነው፤ በሊጉ ከወልዋሎ እና ሀዋሳ ከተማ በመቀጠል ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረው ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የማጥቃት ክፍሉ መዳከም ማሳያ ነው።

በአስራ አራተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ በስድስት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ፍልሚያ ለመዝለቅ ከተከታታይ የሽንፈት ውጤቶች መላቀቅ ግድ ይላቸዋል፤ ይህ እንዲሆንም በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ላሉባቸው ድክመቶች አፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።

የሁለተኛው ዙር ጉዟቸውን በድል የጀመሩት ሻምፕዮኖቹ ንግድ ባንኮች በሀያ አምስት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ድሬዳዋ ከተማን በዘጠኝ ነጥቦች ብቻ የተሰናበቱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአዳማ ከተማ ቆይታቸው አንገታቸው ቀና ማድረግ ችለዋል፤ በድሬ የዘጠኝ ሳምንታት ቆይታቸው አራት ሽንፈት ያስተናገዱት ሀምራዊ ለባሾቹ በአዳማ ከተማ ተመሳሳይ የጨዋታ መጠን አድርገው አንድ ሽንፈት ብቻ ቀምሰው አስራ ስድስት ነጥቦች ሰብስበዋል። ለቡድኑ ውጤት መሻሻል በርከት ያሉ ምክንያቶች ማንሳት የሚቻል ቢሆንም የመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬ ግን በቀዳሚነት ይነሳል፤ የኋላ ክፍሉ በመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች አስራ ሁለት ግቦች በማስተናገድ  ደካማ አጀማመር ማድረግ ቢችልም በአዳማ በተከናወኑ ዘጠኝ ጨዋታዎች ግን በብዙ ረገድ ተሻሽሎ ያተናገዳቸውን ግቦች ወደ አራት ዝቅ ማድረግ ችሏል።

በጣምራ አስራ አራት ግቦች ያስቆጠረው የአዲስ ግደይ፣ ኪቲካ ጅማ እና ሲሞን ፒተር የፊት መስመር ጥምረትም ለቡድኑ መሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን በነገው ወሳኝ መርሐ-ግብርም የተጠቀሱትን ጠንካራ ጎኖች ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

በስሑል ሽረ በኩል ኤልያስ አሕመድ እና አማኑኤል ስንቀይ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም አምበሉ ነፃነት ገብረመድኅንም በግል ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፉዐድ ፈረጃ እና ከሱሌማን ሀሚድ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ተሟልተው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።