ምዓም አናብስት እና ሐይቆቹ የሁለተኛውን ዙር የመጀመሪያ ድል ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች ባለው የውጤት አስፈላጊነት ምክንያት ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለተኛውን ዙር በሽንፈት የጀመሩት መቐለ 70 እንደርታዎች በተከታታይ ካስመዘገቧቸው መልካም ውጤቶች በኋላ የገጠሟቸው ሁለት ሽንፈቶች ወደ አደጋው ክልል ይበልጥ እንዲጠጉ ምክንያት ሆኗቸዋል።
ምዓም አናብስት በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግዱ ከዘለቁ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ማስተናገድ ቢችሉም የመከላከል አደረጃጀቱ አሁንም የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ቡድን የነገ ፍልሚያ ጠንካራ ጎን ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ ሲያደርገው እንደሚስተዋለው በሦስት የመሃል ተከላካዮች አደራደር እና በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የተቃኘ አቀራረብ ይዞ እንደሚቀርብ ሲገመት በሦስት
ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የማጥቃት ክፍል ግን ወደ ቀደመው ጥንካሬው መመለስ ይኖርበታል።
ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ በመጋራት ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በአስራ ስድስት ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፤ ከረዥም ጊዝያት በኋላ ዳግም ወደ ሐይቆቹ ቤት የተመለሱት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ላይ የተቀመጠ እና ጠንካራ ተጋጣሚ ባገኙበት የመጀመርያቸው መርሐግብር አንድ ነጥብ ይዘው በመውጣት መልካም አጀማመር አድርገዋል። ሆኖም የባለፈው ውድድር ዓመት ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ዐሊ ሱሌይማንን ጨምሮ ጥሩ የግብ ማስቆጠር ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች የያዘው እና በሊጉ ከወልዋሎ ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍል የማስተካከል የቤት ሥራ ግን ምናልባትም ለአሰልጣኙ የሚጠብቃቸው ትልቁ የቤት ሥራ ይመስላል። 16 ነጥብ ላይ የሚገኙት ሐይቆቹ በነገው ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በቂ ባይሆንም እንኳን ወደ ማውጫው ለመቅረብ የሚያግዛቸው ነው።
በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐግብሮች በተመሳሳይ ሁለት ግቦች አስተናግደው ግብ ማስቆጠር ያልቻሉ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ በሁለቱም ክለቦች ባለው የውጤት አስፈላጊነት ብርቱ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎም ይጠበቃል።
በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ተመስገን በጅሮንድ እና ክብሮም አፅብሐ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። ላለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ የሰራው ናትናኤል ተኽለ፣ በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው መናፍ ዐወል እና ኪሩቤል ኃይሉም ከጉዳታቸው አገግመው ልምምድ ቢጀምሩም በጨዋታው የመሳተፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በሀዋሳ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት አማኑኤል ጎበና እና ታፈሰ ሰለሞን አገግመዋል፤ በነገው ጨዋታም ከቅጣትም ሆነ ከጉዳት ነጻ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ይቀርባሉ።
ቡድኖቹ ከተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ውጭ በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዋሳ አንድ አሸንፏል፤ ሁለት ጨዋታ ደሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።