ሁለተኛውን ዙር በድል የጀመሩትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የጨዋታ ዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነው።
ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ባቀናበት ጊዜ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ወልዋሎን ካሸነፉ በኋላ በተከታታይ አምስት ተሸንፈው የመጀመሪያውን ዙር ከሲዳማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ያጠናቀቁት አዳማ ከተማዎች ሁለተኛውን ዙር ኤሌክትሪክ ላይ የ2ለ0 ድል በመቀዳጀት ጀምረዋል።
በተሸነፉባቸው አምስት ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ያስተናዱት እና በሊጉ ብዙ ጎሎችን (25) በማስተናገድ ግንባር ቀደም የሆኑት አዳማዎች አራት ነጥቦችን ባሳኩባቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ጎል አለማስተናገዳቸው በተለየም በመከላከል አደረጃጀቱ ላይ ያመጡትን ለውጥ ያሳያል።
ከፍ ብሎ ከሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በሁለት ነጥቦች አንሶ በ19 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በወቅታዊ ድንቅ ብቃት ላይ ከሚገኘው የአዞዎቹ ስብስብ ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ እጅግ የሚጠበቅ ነው።
በ27 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ከ74 በላይ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫውቶ ፋሲል ከነማን 1ለ0 በመርታት እጅግ ወሳኝ የሚባል ድል አሳክቷል።
በጉዳት እና ቅጣት ለሳሳው ስብስብ ሁለት ተጫዋቾችን በአጋማሹ ያስፈረሙት አዞዎቹ በውሰት ፈርሞ በገባበት ጨዋታ 2ኛ ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሮ ተስፋ ሰጥቷቸው የነበረውን ታምራት ኢያሱን 16ኛ ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ ካርድ ማጣታቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።
ከሚጠበቀው በላይ ጉልበት አውጥተው የዐጼዎቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ የገቱት አርባምንጮች የነገው ጨዋታ ከአራት ቀናት በኋላ እንደመደረጉ የማገገሚያ ጊዜያቸው ማጠር በየነገው ጨዋታ ተጫዋቾች ላይ ድካም እንዳይፈጥር የሚያሰጋ ነው። ሆኖም ግን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የሚጫወተውን አዳማ ከተማን ማሸነፍ ወደ አራተኛ ከፍ የሚያደርጋቸው ይሆናል።
በአዳማ ከተማ በኩል ቢኒያም ዐይተን እና ዳግም ተፈራ በነገው ጨዋታ ላይም በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ሳሙኤል አስፈሪ ፣ አበበ ጥላሁን ፣ አሸናፊ ተገኝ ረጅም ጊዜ ከሜዳ ሚያርቃቸው ጉዳት ላይ በመሆናቸው ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን ካሌብ በየነም በጉዳት እና አሸናፊ ፊዳ እና ታምራት ኢያሱ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ቡድኖቹ በሊጉ 17 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 7 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ 4 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አርባምንጭ 14 አዳማ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።