ከዕረፍት መልስ ተቀይሮ በገባው አዲሱ ፈራሚያቸው ዘላለም አበበ ጎል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስሑል ሽረን 1ለ0 በመርታት ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር የመክፈቻ ጨዋታ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድናቸው ውስጥ ስሑል ሽረዎች አብዱለጢፍ መሐመድ ፣ ኤልያስ አህመድ እና ፋሲል አስማማውን በክፍሎም ገብረህይወት ፣ ክፍሎም ብርሀነ እና አሌክስ ኪታታ ሲተኩ መቐለ ላይ ድል ያሳካውን ቡድናቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ለውጥን ሳያደርጉ ቀርበዋል።
ከረር ባለው የአዳማ ፀሐይ ውስጥ ሆኖ የጀመረው የረፋዱ መርሀግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ወረድ ያለ ፉክክር የተመለከተንበት ነበር።
9ኛው ደቂቃ ላይ በንክኪ የተጋጣሚያቸው ሦስተኛ ሜዳ የተገኙት ንግድ ባንኮች ኤፍሬም ወደ ሳጥን ያቀበለውን ኳስ አዲስ ግደይ በማይታመን መልኩ ወደ ውጪ የሰደዳት ኳስ በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ውስጥ ያስተዋልናት መልካሟ አጋጣሚም ሆናለች።
የጨዋታው ደቂቃ ከፍ እያለ ሲመጣ ስሑል ሽረዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው መንቀሳቀሳቸው የጠቀማቸው ንግድ ባንኮች በአንፃራዊነት መሐል ለመሐል በሚሾልኩ እና ከመስመር የሚነሱ ኳሶች ላይ ደጋግመው ትኩረት ባደረጉበት ወቅት ጠንካራ አይሁኑ እንጂ ዕድሎች ጥቂትም ቢሆን ፈጥረዋል።
ያለ ጎል ከተገባደደው የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቅ በኋላ ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ የሚመስል ነገር ግን ደካማ እንቅስቃሴዎች የታከሉበት አጋማሽ በአመዛኙ ሦስተኛው የማጥቂያ ሜዳ ላይ ጥድፊያዎች የበዙበትም ነበር።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛውም ለሳጥኑ የቀረበውን እንቅስቃሴ በማድረጉ የተዋጣላቸው ንግድ ባንኮች በተስፋዬ ታምራት እና ኤፍሬም ታምራት አማካኝነት ካደረጉት ሙከራ በኋላ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች የነበራቸውን ብልጫ ተከትሎ ጎል አስቆጥረዋል።
82ኛው ደቂቃ ኪቲካ ከቀኝ ሳጥን መነሻዋን ያደረገች ኳስን ሳይመን ፒተር ከኋላው ለነበረው እና ከሀላባ ከተማ ከቀናቶች በፊት ቡድኑን ለተቀላቀለው ዘላለም አበበ አቀብሎት አማካዩ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑ በስተመጨረሻም ከጨዋታው ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያሳካ አስችሏል።