አራቱ ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞች ወደ ቦትስዋና ያቀናሉ

አራቱ ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞች ወደ ቦትስዋና ያቀናሉ

በፍራንስ ታውን የሚደረገውን ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለመምራት አራት ኢትዮጵያውያን ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞች ተመድበዋል።በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተካሄዱ ሲሆን ከሞሮኮ ውጪ አራት ሀገራትን ለውድድሩ የምታቀርበው አፍሪካ ተወካዮች ለመሆንም የአፍሪካ ዞን ቡድኖች ሁለተኛ ዙር ማጣሪያቸውን ከጥቂት ቀናት በኋላ ያደርጋሉ።

በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ተጋጣሚዋ ኢኳቶሪያል ጊኒ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ወደ ቀጣይ ዙር በቀጥታ ያለፈችው በአሰልጣኝ አብዴኖር ሚራ የምትመራው ቦትስዋና በሜዳዋ በመጀመሪያው ዙር ቱኒዚያን በድምር ውጤት 1ለ0 አሸንፋ የመጣችውን በአሰልጣኝ ጃኪውላይን ጋይቢኔልዌ የምትመራውን አልጄሪያን ታስተናግዳለች።

ከዋና ከተማዋ ጋቦሮኒ የ436.3 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፍራንሲስታውን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 10 ሰዓት ላይ የሚደረገውን ጨዋታም አራት ኢትዮጵያዊያን ሴት ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲመሩት መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።በዚህም ዋና ዳኛ ማርታ መለሰ ፤ ረዳት ዳኞች ወጋየሁ ዘውዱ እና ይልፋሸዋ አየለ እንዲሁም አራተኛ ዳኛዋ ሲሣይ ራያ ጨዋታውን ለመምራት በነገው ዕለት ወደ ጋቦሮኒ የሚያቀኑ ይሆናል።