የትናንሾቹ ሉሲዎች አሰልጣኝ እና አምበል ከጨዋታው በፊት ምን አሉ?

የትናንሾቹ ሉሲዎች አሰልጣኝ እና አምበል ከጨዋታው በፊት ምን አሉ?

👉 “ሉሲዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸው ለእኛ መነሳሻ ነው የሆነው” አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ

👉 “ዘንድሮ ቡድናችን ውስጥ የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ የምትወስድ ተጫዋች አለች” አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ

👉 “ዓምና ከነበሩት አብዛኞቹ ቋሚ ተጫዋቾች ወጥተውብናል” አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ

👉 “በቡድናችን ውስጥ ጥሩ የማሸነፍ ስሜት አለ ፤ ለጨዋታው ዝግጁ ነን” ህድዓት ካሱ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከካሜሩን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ያደረጉትን ዝግጅት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በቅድሚያም ከየካቲት 13 ጀምሮ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ሆቴል ገብተው በልምምድ ወቅትም ሦስት ተጫዋቾችን በመቀነስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋቸውን የጠቆሙት አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ የተጋጣሚያቸውን የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በቪዲዮ እንደተመለከቱት እና በቆሙ ኳሶች የጎል ዕድሎችን የሚፈጥር ቡድን መሆኑን እንደተረዱ በመግለጽ የተሻለ ነገር እንደሚያደርጉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። የቡድኑ አምበል ህድዓት ካሱ በበኩሏ በቡድናቸው ውስጥ ጥሩ የማሸነፍ ስሜት እንዳለ እና ለጨዋታውም ዝግጁ እንደሆኑ ገልጻለች።

በመቀጠል አሠልጣኝ ራውዳ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ተከታዩን ብለዋል።

“የተጫዋቾች ምርጫ ከውድድር ስለራቁ ቀድመን ከዚምባቡዌ ለነበረን ጨዋታ በቴሌግራም ግሩፕ ከፍተን ልጆች እንዲንቀሳቀሱ ከዛም በኋላ ትሬኒንግ እየሰጠኋቸው ተንቀሳቅሰው ወደእኔ የሚልኩበት አጋጣሚ ነበር። አብዛኛው የዕድሜ እርከን ውድድር በጣም አስቸጋሪ ነው ፤ ከዓምናው ከነበሩት አብዛኞቹ ቋሚ ተጫዋቾች ወጥተውብናል። ልጆችን ለመመልመል ረጅም ጊዜ ሰጥቻለሁ እኛ ሀገር ከ17 ዓመት በታችም ሆነ የትምህርት ቤት ውድድር ስለሌለ ከፕሪሚየር ሊግ እና ከሱፐር ሊግ ነው የያዝኩት እና ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው በትክክለኛ ዕድሜ ላይ ናቸው። ዘንድሮ ቡድናችን ውስጥ ከጥሩነሽ አካዳሚ ያገኘናት የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ የምትወስድ ሊዲያ ኢያሱ የምትባል ልጅ አለች። የወዳጅነት ጨዋታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያደረግነው ከካሜሮን ጋር ተቀራራቢ ነገር ይኖራቸዋል በሚለው ነው። ጥሩ ልምድ ነው ያገኘነው። ዋናው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉ ለእኛ መነሳሻ ነው የሆነው። ተጫዋቾችም እዛው ቦታው ላይ ሆነው ስላዩ ለሀገር የተሻለ ነገር ለመሥራት ለሀገር መጫወት ያለውን ስሜት በማየት ዋናው ቡድን ውስጥ ለመግባት ተነሳሽነቱ አላቸው። የእነሱ ማሸነፍ ለእኛ ግብዓት ነው የሆነው። ለእኛ እንደ አሰልጣኝም እንደ ባለሙያም መማሪያ ነው የሆነው።