በመጀመርያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ የተገናኙት ዐፄዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ የሚፋለሙበት ተጠባቂው ደርቢ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ነው።
የመጀመሪያውን ዙር በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች በሀያ ሦስት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ላይ ከተቀዳጃቸው ወሳኝ ድሎች በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ወደ አደጋው ክልል ቀርቧል፤ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል ይዞባቸው ከሚመጣው ስጋት ለመላቀቅም ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ የመውጣት ግዴታ አለባቸው።
መጠኑ ይለያይ እንጂ ፋሲሎች በሊጉ ዘንድሮ ያደረጓቸው አብዛኞቹ ጨዋታ በተመሳሳይ መገለፅ የሚችሉ ናቸው፤ ቡድኑ በአመዛኙ ጨዋታዎቹ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም የግብ ዕድሎች መፍጠር እና እንዲሁም የሚገኙትን ዕድሎች በአግባቡ የመጠቀም ድክመት ይስተዋልበታል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ዕለት በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐ-ግብሮች ስድስት ግቦች ላስቆጠረው እና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ለሚገኘው የጣና ሞገዶቹ የማጥቃት ክፍል የሚመጥን የመከላከል ውቅር ከማበጀት በዘለለ በአዞዎቹ ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ከመልካም እንቅስቃሴ በዘለለ ንፁህ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገረው አቀራረባቸው ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ለሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ሳያደርጉ ከዘለቁ በኋላ የነገው ተጋጣሚያቸው ፋሲልን ጨምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡት የጣና ሞገዶቹ በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ተጠባቂ በነበረው የመጨረሻው መርሀ-ግብር ፈረሰኞቹ ላይ አራት ግቦች አስቆጥረው ድል ያደረጉት ባህርዳሮች በቅርብ ሳምንታት በአፈፃፀሙ ረገድ ጉልህ መሻሻሎች አሳይተዋል፤ ተከታታይ ድል ካስመዘገበባቸው መርሐ-ግብሮች በፊት በስድስት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው ቡድኑ ጠንካራ የኋላ ክፍል ካላቸው ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ግን ስድስት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ቡድኑ በስድስት ጨዋታ ካስቆጠረው የግብ መጠን የሚልቅ በሁለት ጨዋታ ከማስቆጠሩ በላይ ግቦቹ ጠንካራ የኋላ ክፍል ባላቸው ቡድኖች የተቆጠሩ መሆናቸውም የፊት መስመሩ አሁናዊ ጥሩ ብቃት ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በጣምራ አምስት ግቦች ባስቆጠሩት ቸርነት ጉግሳ እና ባለ ‘ሀትሪኩ’ ወንድወሰን በለጠ የሚመራው የጣና ሞገዶቹ የማጥቃት ክፍል ከዐፄዎቹ የተከላካይ ክፍል የሚያደርጉት ፍልምያ ከደርቢ ስሜቱ በተጨማሪ ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ወሳኙ ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ በ10 ቢጫ ካርዶች ምክንያት በተላለፉበት የሁለት ጨዋታ ቅጣቶች በነገው ጨዋታ ላይ አይኖርም። በፋሲል ከነማ በኩል ከሀቢብ መሐመድ ውጪ በጉዳትም ሆኖ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 11 ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 7 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ ባለድል መሆን ችለዋል። በጨዋታዎቹ ዐፄዎቹ 9 ግቦች እንዲሁም የጣናው ሞገድ ደግሞ 6 ጎሎችን አስቆጥረዋል።