ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

በሁለት ነጥቦች እና በሦስት ደረጃዎች ልዩነት የተቀመጡት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።

ከስምንት ሽንፈት አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ተከታታይ ሽንፈት የገጠማቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ፈረሰኞቹ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አንዱን ብቻ በማሳካት በደካማ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በተከታታይ ጨዋታዎች በተቀዳጃቸው ድሎች በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የነበረው ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በኋላ አሁንም በፉክክሩ ውስጥ ይገኛል። ሆኖም የቀደመው የራስ መተማመን መንፈሳቸውን ለመመለስ እና በፉክክሩ ለመዝለቅ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ የመውጣት ፈተና ይጠብቃቸዋል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ማስተካከል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል፤ በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ተጋላጭ የነበረው ቡድኑ በሽግግሮች ለማጥቃት ጥረት ከሚያደርጉት የጦና ንቦቹ በሚገጥምበት ጨዋታ ክፍተቶቹን ካላስተካከለ ወደ መከላከል ከሚደርገው ደካማ ሽግግር አንፃር ለጥቃት መጋለጡ የሚቀር አይመስልም።

በሀያ ሰባት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል በሁለት ነጥቦች እና በሦስት ደረጃዎች ልቆ የተቀመጠውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ይገጥማሉ።

በመጨረሻው መርሐ ግብር መሪው መድን ላይ ድል የተቀዳጁት የጦና ንቦቹ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች  አገግመው ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከሽንፈት ከመራቃቸው በዘለለ በሦስቱ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን በማሳካት በጥሩ ወቅታዊ አቋም ይገኛሉ።  አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ከአርባምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍላቸው ላይ ማስተካከያዎች ማድረጋቸው ቡድኑን ወደ ውጤት ጎዳና መልሶታል። ከተጠቀሱት ጨዋታዎች በኋላ በተካሄዱ ሦስት መርሐ ግብሮች በሁለቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ የመከላከል አደረጃጀቱን ጥንካሬ ማስቀጠል ከነገው ጨዋታ ውጤት ይዞ እንዲወጣ ያስችለዋል።

በሽግግሮች እንዲሁም በቀጥተኛ አጨዋወት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐ-ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ያለማስቆጠራቸው የሚያሳስባቸው ጉዳይ ይመስላል፤ በቀጣይም የግብ መጠኑን ከፍ ለማድረግ የሚፈጥሯቸው የጠሩ የግብ ዕድሎች ቁጥር ከፍ የማድረግ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነው ስብስብ ይዘው ለጨዋታው ይቀርባሉ። በወላይታ ዲቻ በኩልም የብዙአየሁ ሰይፉ የመሰለፍ ጉዳይ አጠራጣሪ ከመሆኑ በስተቀር የተቀረው የቡድኑ አባላት ለጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች 21 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ወላይታ ድቻ 6 ድሎችን አሳክተዋል። አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 28 ወላይታ ድቻ ደግሞ 16 ጎሎች አስቆጥረዋል።