ሪፖርት | ፋሲል እና ባህር ዳርን ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

ሪፖርት | ፋሲል እና ባህር ዳርን ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በሳምንቱ ተጠባቂ የነበረው የዐፄዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ የደርቢ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

በኢዮብ ሰንደቁ

ፋሲል ከነማዎች በአርባምንጭ ከተማ 1-0 ከተረቱበት ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ ላይ የነበሩትን ሸምሰዲን መሀመድ ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና አንዋር ሙራድን በማሳረፍ በምትካቸው ኪሩቤል ዳኜ ፣ ኢዮብ ማቲያሰ እና ቢኒያም ጌታቸውን ሲያስገቡ በተቃራኒው ባህር ዳር ከተማዎች በጎል ተንበሽብሸው ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፉበት ጨዋታ የሁለት ተጨዋቾች ቅያሪ አድርገው ፍሬዘር ካሳን በፍፁም ፍትሕዓለው ፣ ሄኖክ ይበልጣልን ደግሞ በፍቅረሚካኤል ዓለሙ በመቀየር ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ከቀኑ 9 ሰዓት ሲል በፌዴራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ስታዲየም የተጀመረው ተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ሰዓት ድረስ ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን በሁለቱም ቡድኖች መካከል ያሳየን ነበር። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አስፈሪነታቸውን ያሳዩት የባህር ዳር ከተማ አጥቂዎች እንደወትሮው ሁሉ በቁጥር በዛ በማለት በመስመር የሚነሱ ኳሶችን ቀዳሚ የማጥቂያ አማራጭ በማድረግ የፋሲል ተከላካዮችን ሲፈትኑ ተስተውለዋል።

የባህርዳር ከተማዎች የማጥቃት ዒላማ የሆነው ቸርነት ጉግሳ 20ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የፋሲል ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ሳጥን ውስጥ የሰጠው ኳስ ኃይል ከመብዛቱ የተነሳ ወንደሰን በለጠ ሊደርስበት ባለመቻሉ በጣና ሞገዶች በኩል አስቆጪ ዕድል ነበር። በሌላ አጋጣሚ 30ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ከሳጥን ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፋሲል ሲመልሰው ያንኑ የተመለሰውን ኳስ ወንድወሰን በለጠ በድጋሚ ቢሞክረውም ፋሲል ገብረሚካኤል ይዞበታል።

ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደጋግመው መድረስ የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች 41ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ የግል ክህሎቱን በመጠቀም ከመሃል ሜዳ በመነሳት ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ይዞት የገባውን ኳስ ቢሞክረውም ሚዛኑን በመሳቱ ምክንያት ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ላይ ከወንድሜነህ ከርቀት የተሻገረለትን ኳስ ያገኘው ፍፁም አለሙ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ መትቶ የሞከረውን ኳስ ፋሲል ገብረሚካኤል ወደ ውጭ በማስወጣት ግብ ከመሆን ታድጎታል።

የመጀመሪያውን አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በኳስ ቁጥጥር በልጠው ሲጫወቱ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች ብልጫውን ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ በመቅረታቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽለው በጥሩ መነቃቃት ወደ ሜዳ የተመለሱት ዐፄዎቹ በኳስ እና በተጋጣሚ ቁጥር ብልጫ በውሰድ ተጭነው ማጥቃት የቻሉ ሲሆን በዚህም የተነሳ 58ኛው ደቂቃ ላይ ማርቲን ኪዛ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ቢኒያም ጌታቸው ቢመታውም ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበት ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ፋሲል ከነማወች የሜዳው መሃል ክፍል ላይ ብልጫ በመውሰድ በኳስ ቁጥጥሩ እና እንቅስቃሴው ረገድ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ግን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ካገኙት ፍፁም ቅጣት ምት በስተቀር ምንም አይነት ዒላማውን የጠበቀ የጎል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ሙከራ ሳያስመለክተን በቆየው ሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቆዩት ባህር ዳር ከተማዎች ቀይረው ባስገቧቸው ተጨዋቾች ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለው ነበር። በ86ኛው ደቂቃ ላይ  በአንድ ሁለት ቅብብል አቤል ለ ሔኖክ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ሔኖክ ወደ ጎል ቢሞከረውም ፋሲል ገብረሚካኤል መልሶበታል ያንኑ የተመለሰ ኳስ አቤል እግር ስር ቢያርፍም መጠቀም ሳይችልበት ወደ ውጭ ወጥቷል።

ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ያሳየን እና የሳምንቱ ተጠባቂ የነበረው የደርቢ ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።