ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቻል ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቻል ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

የ21ኛው ሳምንት ጨዋታቸው በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት መቻል እና ወልዋሎ ከሳምንታት በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

ከድል ጋር ከተኳረፉ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት መቻሎች ከነበሩበት ደረጃ  ርቀው በሰንጠሩዡ ወገብ ላይ ይገኛሉ። በሂደት በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ካለው ፉክክር በመራቅ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቻል ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ብቻ ማሳካቱ ደረጃውን አሳጥቶታል። መቻል በሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ከገጠሙት ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ በመጨረሻው ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም ለግብ ማስቆጠር ችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት አልቻለም። ከአርባምጭ ከተማ ጋር በጣምራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በቀደመ ጥንካሬው አይገኝም። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት አጨዋወት ላይ ስር ነቅል ለውጦች ማድረግም የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በደካማ አጀማመር ተከታታይ ሽንፈቶችን አስተናግዶ  በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የተቀመጠው ወልዋሎ በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መሻሻሎች አሳይቶ ከተከታታይ ሽንፈቶች ቢርቅም ለሃያ አንድ ሳምንታት ከግርጌው መላቀቅ አልቻለም። በሊጉ ስምንት ነጥቦች መሰብሰብ የቻለው ቡድኑ በነገው ዕለት ድል ማድረግ በ17ኛ ደረጃ ላይ ካለው ስሑል ሽረ ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ የሚያደርግለት እንደመሆኑ በቀላሉ አይመለከተውም። በዝውውር መስኮቱ ሳሙኤል ዮሐንስ፣ ሐብታሙ ንጉሴ፣ ሙሳ ራማታህ እና ፉሀድ አዚዝ ያስፈረሙት ቢጫዎች በነገው ዕለት ሐብታሙ ንጉሴን በጨዋታ ስብስቡ ያካትታሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከቼክ ሪፓብሊኩ  ‘ኤም ኤፍ ኬ ቪስኮቭ” የፈረሙት ዩጋንዳዊያን ግን በነገው ጨዋታ የመሰለፋቸው ጉዳት አልለየለትም።

በመቻል በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ የነበረው አምበሉ ምንይሉ ወንድሙ ከጉዳቱ በማገገሙ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ታውቋል። በወልዋሎ በኩል ኪሩቤል ወንድሙ ከቅጣት ሲመለስ ዮናስ ገረመው አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ በነገው ጨዋታ አይሳተፍም።

በፕሪምየር ሊጉ 5 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱም ክለቦች መቻል 3 ጊዜ ድል ሲቀናው ወልዋሎ 2 ጊዜ አሸንፏል፤ በጨዋታዎቹም መቻል 6 ወልዋሎ ደግሞ 3 ግቦች አስቆጥረዋል።