የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ወላይታ ድቻ

የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ወላይታ ድቻ

👉”ጥሩ ዝግጅት አድርገን በመምጣታችን በአሸናፊነት መጨረስ ችለናል” አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ

👉 የጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ የአሰልጣኝ አስተያየት ሳይሰጥ ሄዷል።

ወላይታ ድቻ በአብነት ደምሴ ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

በጣም ቆንጆ ጨዋታ ነበር። ተፎካካሪያችንም ጠንካራ ቡድን ነው። ባለፈው ተሸንፎ ነው የመጣው። ጥሩ ዝግጅት አድርገን በመምጣታችን ውጤቱን በአሸናፊነት ለመጨረስ ችለናል።

ስለቆመ ኳስ አጠቃቀም

ዝግጅት አርገንበታል። ብዙ ጊዜ የቆሙ ኳሶችን እየተጠቀምን አልነበረም፤ካለፈው ጌም ጀምሮ በቆመ ኳስ ውጤታማ እየሆንን መጥተናል። በተደጋጋሚ የተጠናከረ ስራ ሰርተን መተን ጎል አግኝተናል።

ስለመከላከል አደረጃጀቱ

ጥሩ ነው። ከከፍተኛ ሊግ ያመጣነውም ተጫዋች ጨዋታዎችን አይቶ ወደ ውድድር ስለገባ ከቀን ወደ ቀን ልምዱን እያሻሻለና እየጠነከረ እንዲሁም የነበሩት የእኛ ልጆች እየተለዋወጡ እየተተካኩ ጉልበታቸውን ቆጥበው እየተጫወቱ ነው። ካለፈው ዓመት በተሻለ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ ነው። በዚሁ ከቀጠሉ ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ነገር ማየት እንችላለን ብዬ አስባለው።

ስለቀጣዩ ጨዋታ

ዓለም ላይ ታች ግርጌ ናቸው ተብለው የተናቁ ቡድኖች መሪውን እያሸነፉ አይተናል። ለእኔ እንደውም ከባዱ ጨዋታ የቀጣዩ የወልዋሎ ጨዋታ ነው። ከባድ ትግል እና ፈተና የሚጠብቀን ጨዋታ ነው። ለዛ ደግሞ ከፍተኛ ዝግጅት አርገን መምጣት አለብን።

ለወትሮ እንደ ሌሎቹ አሠልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየት የሚሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን ሳይሰጡ ከስታዲየም ወጥተዋል።